
ባሕር ዳር: ነሐሴ 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር እየተከናወኑ ያሉት የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራት እንደቀጠሉ ናቸው። የአራት አረጋውያንን ቤት ሙሉ በሙሉ በማፍረስ በአዲስ ለመገንባት ስድስት ተቋማት በአንድ ላይ ሥራ ጀምረዋል። የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ፣ በከተማው የሚገኙ ሦስቱ ጤና ጣቢያዎች፣ የደብረ ታቦር ከተማ ሆስፒታል እና የደብረ ታቦር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ናቸው ቤቱን እየገነቡ የሚገኙት።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኅላፊ በረከት ገደፋው እንደገለጹት የተለያዩ ተቋማትን በማስተባበር የአራት አረጋውያንን ቤቶች በአዲስ ለመሥራት ከ150 ሺህ ብር በላይ ማሰባሰባቸውን ገልጸዋል። ወቅቱ ክረምት ከመኾኑም በላይ ቤቶቹ በከፍተኛ ሁኔታ ስለፈራረሱ እና ለነዋሪዎች አስቸጋሪ ኾነው በመመልከታቸው ቤቶቹን ለማደስ መነሳሳታቸውን ገልጸዋል። በጎነት ለሁሉም የሚበጅ ስለኾነ ሁሉም ተሳትፎ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
ከደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ኮሙኒኬሽን መምሪያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ቤት የሚገነባላቸው አረጋውያን እየተሠራላቸው ባለው የበጎ ፈቃድ ሥራ ከችግር የሚያወጣቸው እንደኾነ በመግለጽ ለተደረገላቸው በጎ ተግባርም ምሥጋናቸውን አቅርበዋል። የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን በጎነት በምንም የማይተመን የመንፈስ እርካታን የሚሰጥ ከመኾኑም በላይ በዚህ አይነት በጎ ተግባራት መሳተፍ ትልቅ ማኀረሰባዊ እሴትን የሚያጎለብት እንደኾነ ተናግረዋል። “በበጎነት በሚሠሩ ሥራዎች የበርካታ የማኀበረሰብ ችግሮችን ይቀርፋሉ” ያሉት ከንቲባው ሁሉም ሰው ባለው አቅም ለበጎነት መሥራት እና መተባበር እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኅላፊ እሸቱ ውለታው ”በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ መልእክት የተጀመረውን የ2016/17 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ ተከትሎ በከተማዋ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደኾነ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!