
ባሕር ዳር: ነሐሴ 09/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአድርሽኝ በዓል የፍልሰታ ጾምን ተከትሎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በስፋት የሚከበር በዓል ነው። በዓሉ የፍልሰታ ጾም ከገባ ነሐሴ 1 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 16 ባሉት ተከታታይ ቀናት ውስጥ ከጾሙ ጋር አብሮ ይዘከራል።
አድርሽኝ በማኅበር ደረጃ የሚከበር ሲኾን የማኅበር አባላት ከነሐሴ 1 እስከ 16 ያሉትን ቀናት ተከፋፍለው በየተራ በሚያዘጋጁት ዝክር አማካኝነት የሚከበር ይኾናል። የአድርሽኝ በዓል ከሃይማኖታዊ ገጽታው ባለፈ ሰው ከሰው የሚጠያየቅበት፣ ጎረቤት የሚገናኝበት እንዲሁም ማኅበረሰቡ ማኀበራዊ ትሥሥሩን የሚያጠናክርበት ባሕላዊ ትውፊትም አለው።
ጎንደር ከተማ የሚገኘው የኪዳነ ምህረት አድርሽኝ ማኀበር ለባለፉት 30 ዓመታት የቆየ ማኀበር ነው። ማኀበሩ በአሁኑ ወቅት 14 አባላቶች ያሉት ሲኾን አባላቱ በዓሉን በቆሎ፣ በዳቦ እና በባሕላዊ መጠጦች ይዘክሩታል። የማኀበሩ አባል የኾኑት ሰይፈሥላሴ ኃይሉ የአድርሽኝን በዓል ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ሥርዓቱን እንደጠበቀ እያከበሩ መኾኑን ያብራራሉ።
የማኀበሩ ሊቀመንበር ወጣት ማሩ ደግሞ በዓሉ ማኀበራዊ ትሥሥርን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ይናገራል። ማኀበሩ በአድርሽኝ በዓል ሆስፒታል በመሄድ የታመሙትን ይጠይቃል፣ አቅመ ደካሞችን ይረዳል፣ መጪው የትምህርት ዘመንን ምክንያት በማድረግ ለተቸገሩ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ እና ዩኒፎርም ይገዛል።
በጎንደር ከተማ የመንበረ መንግሥት የድጓ መምህር እና በከተማዋ ባሕረ ጥበብ ሁለገብ የሀገር በቀል ትምህርት ቤቶች መምህር የኾኑት ቀለመወርቅ ደምሌ አድርሽኝ ሃይማኖታዊ መሠረት እንዳለው ያብራራሉ። እንደ እሳቸው ማብራሪያ “አድርሽኝ ድንግል ማርያም የምትታሰብበት እና የምትዘከርበት በዓል ነው”። የእምነቱ ተከታዮች ድንግል ማርያም በሰላም ካደረስሽኝ እዘክርሻለሁ ብለው ከተሳሉ በኃላ በዓመቱ በሰላም ሲደርሱ ቀኑን ይዘክሩታል።
ክርስቶስን የወለደች ድንግል ማርያም ዝክርሽን የዘከረ፣ ስምሽን የጠራ፣ በስምሽ የዘከረን ሁሉ እምረዋለሁ ተብሎ ቃልም ስለተገባላት ምዕመናንም ከፈጣሪ ምህረት እና ፀጋን በማሰብ የአድርሽኝን በዓል እንደሚያከብሩት ያስረዳሉ። ከዚህ ሃይማኖታዊ መሠረት በተጨማሪም በተለይ በጎንደር ከተማ አድርሽኝ በስፋት የሚከበርበትን ታሪካዊ መሠረትም ገልጸውልናል።
በጎንደር ዘመነ-መንግሥት የልደታ ለማሪያም ቤተክርስቲያን መሥራች የነበሩት አጼ ዮስጦስ ወደ ዘመቻ ይሄዳሉ። ወደ ዘመቻው ሲሄዱም በሰላም ከተመለስኩ የፍልሰታ ጾምን እጾማለሁ፣ ዝክርሽን እዘክራለሁ ብለው ተስለው ነበር። ዘመቻው ተጠናቆ አጼ ዮስጦስ ከዘመቻ በሰላም ተመለሱ። በዚህም ምክንያት አጼ ዮስጦስ የማርያምን ተዓምር ለሕዝቡ እየተናገሩ፣ አድርሽኝ እያሉ፣ በዓሉ በተለይ በጎንደር በስፋት እንዲከበር አድርገዋል ይላሉ መምህር ቀለመወርቅ ደምሌ።
የአድርሽኝ በዓል ሃይማኖታዊ መሰረቱን እንደያዘ በማኀበረሰቡ ውስጥ ልዩ ባሕላዊ ገጽታን ተላብሶ እየተከበረ ስለመኾኑም መምህሩ ያብራራሉ። በመጨረሻም መምህር ቀለመወርቅ ደምሌ በዓሉ የበረከት፣ የድኅነት እና የአንድነት እንዲኾን ተመኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!