
ባሕር ዳር: ነሐሴ 9/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተደራሽ፣ ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢ እና የተገልጋዮችን እንግልት ለመቅረፍ የሚያስችል የዳኝነት አገልግሎትን ለማረጋገጥ ያለመ የሥራ ጉብኝት ማካሄዱን ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው የተመራ ልዑክ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ከነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሲያከናውን የነበረው የሦስት ቀናት የሥራ ጉብኝት መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡
የልዑካን ቡድኑ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሙሉዓለም ቢያዝንን ጨምሮ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት፣ ከአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ኮሚሽን፣ ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሪዎች እንዲሁም ከባለሙያዎች የተካተቱበት ነበር፡፡
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው የጉብኝቱ ዋና ዓላማ በክልል ደረጃ የተያዘው የፍትሕ ተቋማት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አካል የኾነውን የተቀናጀ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጅ ፕሮጄክትን በክልሉ ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ በማድረግ ተደራሽ፣ ቀልጣፋ፣ ወጭ ቆጣቢ እና የተገልጋዮችን እንግልት በመሠረታዊነት ለመቅረፍ የሚያስችል የዳኝነት አገልግሎት ለማረጋገጥ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረጃ የተደረገውን የቴክኖሎጅ መሠረተ ልማት እና የአገልግሎት ዳሰሳ ጥናት ውጤታማ ስለመኾኑ ነው ያስረዱት፡፡ ከፌዴራል ተቋማት የተገኘውን ልምድ እና በክልሉ ያለውን አቅም ሁሉ በመጠቀም የዳኝነት አገልግሎቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጅ የታገዘ ለማድረግ እንዲቻልም የሥራ ቡድን ተቋቁሞ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!