ግብር ከፋዮች ለአላስፈላጊ ቅጣት እና መጉላላት እንዳይዳረጉ ሕጉን ተከትለው በወቅቱ ግብራቸውን እንዲከፍሉ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አሳሰበ፡፡

8

ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው አዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 1341/2016 ዙሪያ የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፍቅረማርያም ደጀኔ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በነባሩ የተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1157/2011 አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 1 የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢዎች የሂሳብ ጊዜ ከ70 ሚሊየን ብር በላይ ዓመታዊ ገቢ ለነበራቸው በየወሩ እንዲሁም ከዛ በታች ለሆኑ በየ3 ወሩ ታክስ ሒሳብ ሲያሳውቁ መቆየታቸው ይታወቃል። ይሁን እንጅ በአዲሱ አዋጅ መሠረት በየወሩ ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው መደንገጉን ኀላፊው ተናግረዋል፡፡

ሌላው አዋጁ ያሻሻለው የተጨማሪ እሴት ታክስ ለመመዝገብ ዓመታዊ ግብይት ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የነበረው ወደ 2 ሚሊዮን ብር ከፍ ብሎ መሻሻሉንና ዓመታዊ ግብይታቸው ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ግብር ከፋዮች በፈቃደኛነት ለተጨማሪ እሴት ታክስ መመዝገብ ይችላሉ ብለዋል፡፡

በክልሉ 18 ሺህ 806 የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢዎች ሪፖርት ማድረግ የሚጠበቅባቸው ግብር ከፋዮች እንዳሉም ተናግረዋል። በአዲሱ አዋጅ መሠረትም ሐምሌ ወር ላይ የተከናወኑ ግብይቶች እስከ ጳጉሜን 5/2016 ዓ.ም እንዲሁም ነሐሴ ውስጥ የተካሔደን ግብይት እስከ መስከረም 30/2017 ዓ.ም ሪፖርት ማድረግ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡

ግብር ከፋዮች ለአላስፈላጊ ቅጣት እና ወለድ እንዳይዳረጉ ሕጉን ተከትለው በተሰጣቸው ጊዜ በየደረጃው በሚገኝ የገቢ ተቋም ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

አቶ ፍቅረማርያም አያይዘውም የ2017 በጀት ዓመት የደረጃ “ሐ” ግብር አሰባሰብን በተመለከተ መረጃ ሰጥተዋል። በክልሉ 359 ሺህ 057 በላይ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ባለው ነባራዊ ሁኔታ 262 ሺህ 735 ግብር ከፋዮች ግዴታቸውን ይወጣሉ ተብለው ተለይተው 165 ሺህ 193 የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች እና 44 ሺህ 713 የኪራይ ገቢ ግብር ከፋዮች በድምሩ 209 ሺህ 906 ግብር ከፋዮች በሐምሌ ወር ያለምንም ቅጣትና ወለድ ግብራቸውን ከፋለዋል ብለዋል፡፡

ሁሉም ለገቢ አሰባሰቡ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የሚዲያ አካላት ግንዛቤ በመፍጠር እና የፀጥታ አካላት ለገቢ ተቋሙ አጋር በመሆን እያደረጉ ላሉት አስተዋፅኦ አቶ ፍቅረማርያም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ መረጃው የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአጣየ ከተማ የተጀመረው የሰላም ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁላችንም በጋራ እንድንሠራ ጥሪየን አቀርባለሁ” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)
Next articleተደራሽ እና ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የሥራ ጉብኝት ማድረጉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።