በጥራት ተወዳዳሪ የኾኑ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ለማምረት እየሠራ እንደሚገኝ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።

20

ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ወጭዎችን ለመቀነስ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ማምረት እንዳለባት ይታመናል፡፡ በሂደቱም በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ጥራታቸውን አሳድገው በማኀበረሰቡ ዘንድ ተመራጭ እና ተወዳጅ እንዲኾኑ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪ እና የኢንቨስትመንት መምሪያ ኅላፊ ብርሃን ንጉሴ በከተማ አሥተዳደሩ 657 የሚኾኑ ባለሀብቶች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሬት ወስደዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 207 ባለሃብቶች ሥራቸዉን ጨርሰዉ ወደ ማምረት የገቡ ናቸው፡፡ ሌሎቹ በልዩ ልዩ የግንባታ ሂደት ውስጥ እና ማሽን በማስገባት ላይ ይገኛሉ።

በከተማ አሥተዳደሩ የሚመረቱ ምርቶች ጥራት ኖሯቸዉ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ለማድረግ ኢንዱስትሪዎች የሠለጠነ የሰው ኃይል እንዲጠቀሙ እየተሠራ እንደኾነ ወይዘሮ ብርሃን ተናግረዋል፡፡ የተማረ እና የሠለጠነ የሰዉ ኃይል ለመቅጠር ከባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ጋር በመቀናጀት በጋርመንት የሠለጠኑ ልጆች እንዲቀጠሩ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል፡፡

የሀገር ውስጥ ምርትን መጠቀም ላይ የኀብረተሰቡ አመለካከት መቀየር አለበት ያሉት የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኅላፊ እንድሪስ አብዱ በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የተሻለ ምርት እንዲያመርቱ ከሚመለከታቸዉ አጋር አካላት ጋር ቢሮዉ እየሠራ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ ኢንዱስትሪዎች በጥራት ፣ በብዛት እና በፍጥነት እንዲያመርቱ ቢሮው ክትትል እና ድጋፍ እያደረገ እንደኾነም ነዉ የገለጹት፡፡

በአማራ ክልል ከ3 ሺህ በላይ አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች አሉ፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአንድነት እና አብሮነት የሚያጠናክሩ ሥራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሠራ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next article“በአጣየ ከተማ የተጀመረው የሰላም ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁላችንም በጋራ እንድንሠራ ጥሪየን አቀርባለሁ” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)