
ባሕር ዳር: ነሐሴ 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የተመራ ልዑክ በደሴ ከተማ የችግኝ ተከላ እና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አካሂዷል፡፡ አንጋፋ እና ታዋቂ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የሕዝብ ተወካዮች፣ የክልል እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች በመርሐ ግበሩ ላይ ተሳትፈዋል።
የባሕል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ እና ለአቅመ ደካሞች ማዕድ ማጋራቱን ገልጸዋል፡፡ በበጎ ፈቃድ የቤት እድሳት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉንም አንስተዋል፡፡ ገንዘቡ በቂ ስላልኾነ የተጀመረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማጠናከር ተጨማሪ ድጋፎች እንደሚኖሩም ገልጸዋል፡፡
እንደ ሀገር የሕዝብን አብሮነት እና አንድነት ለማጠናከር በበጀት ዓመቱ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑ የገለፁት ሚኒስትሯ ለዚህም የኪነ ጥበብ ሰዎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ ሚኒስትሯ በታሪካዊው የመምህር አካለወልድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአረንጓዴ አሻራ አስቀምጠዋል፡፡
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋየ የተጀመሩትን የበጎ ፈቃድ ሥራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል ቢሮው የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ያለውን እምቅ ባሕል በማጉላት የዜጎችን ትሥሥር ለማጠናከር ይሠራልም ነው ያሉት፡፡ ኪነ ጥበብ የሕዝብን ፍቅር እና አንድነት አጉልቶ በማውጣት ያለውን ከፍተኛ ሚና በመጠቀም የኪነ ጥበብ ሰዎች የራሳቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ የተሳተፉት የኪነ-ጥበብ ሰዎችም በሙያቸው ሰላም፣ ፍቅር፣ አብሮነት እና አንድነትን በማጉላት የሕዝቦችን የመተባበር መንፈስ ለማጠናከር እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀን አምባቸው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!