በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ሥራ አሥፈፃሚዎች ሥነ ምግባርን በመላበስ በተገቢው መንገድ ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ ተጠየቀ።

11

ደብረ ማርቆስ: ነሐሴ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የመምሪያ፣ የክፍለ ከተማና የቀበሌ አመራሮች በ2017 ዓ.ም የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች ዕቅድ ዙሪያ ውይይት እያደረጉ ነው።

በውይይቱ መክፈቻ ላይ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ የ2016 በጀት ዓመት በበርካታ ፈተናዎችም ውስጥ ኾነን አበረታች ስኬቶች ያስመዘገብንበት ነው ብለዋል። በበጀት ዓመቱ በከተማዋ የተዘረጋውን የመንገድ ዳርና የዓደባባይ ልማት እንደ አብነት አንስተዋል፡፡

ሕዝብን ያማረሩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችና ብልሹ አሠራሮች አሁን ላለንበት ፈተና ዳርገውናል፤ ያሉት ከንቲባው በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ሥራ አስፈፃሚዎች ሥነ ምግባርን በመላበስ በቅንነት ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉም አሳስበዋል ።

በ2016 የታዩ ጥንካሬዎችን ማስቀጠልና ጉድለቶችን መሙላት እንደሚገባም አስገንዝበዋል ።

በመንቆረር ክፍለ ከተማ የቀበሌ 05 ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ኤርሚያስ ጌታነህና የተድላ ጓሉ ክፍለ ከተማ፣ ከተማና መሠረተ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስለሺ ፈንቴ በ2016 በጀት ዓመት በሰላም መደፍረስ ምክንያት በርካታ ቁሳዊና ሰብዓዊ ጉዳት ያስተናገድንበት ቢኾንም የኅብረተሰቡን የመልካም አሥተዳደደርና የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት ጥረቶች ስለመደረጋቸው ገልጸዋል ፡፡

አገልግሎት አሰጣጡን ከእጅ መንሻ ነጻ ማድረግና ኅብረተሰቡን በኃላፊነት ስሜት ማገልገል የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ሊኾኑ ይገባልም ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ከተማ አሥተዳደሩ አስታወቀ፡፡
Next articleአንድነት እና አብሮነት የሚያጠናክሩ ሥራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሠራ የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።