ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ከተማ አሥተዳደሩ አስታወቀ፡፡

82

ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ደብረ ታቦርን በደብረታቦር ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ከተማ አሥተዳደሩ አስታውቋል፡፡ የታሪክ፣ የሃይማኖት፣ የባሕል እና የእሴት ባለቤት የኾነችው ደብረ ታቦር የቡሔ እና የመርቆሪዎስን በዓል በድምቀት በማክበር ትታወቃለች፡፡

የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ መንደር የጋፋት መገኛ፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጅ መጠንሰሻ፣ የአጼ ቴዎድሮስ ራዕይ መፈንጠቂያ፣ ደብረ ታቦር አያሌ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ሃብቶችን ይዛለች፡፡ ከተማዋ በብዙዎች ዘንድ ቡሔ እየተባለ የሚጠራውን የደብረ ታቦርን በዓል እና የቅዱስ መርቆሪዎስን በዓላት በድምቅት በማክበር ልዩ መገለጫወቿ አድርጋቸዋለች፡፡

ከቀናት በኋላ የሚከበረውን የደብረ ታቦርን በዓል በደብረታቦር ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን የከተማ አሥተዳደሩ ባሕል እና ቱሪዝም ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ ከተራራው አናት ላይ በሚገኘው በጥንታዊ የኢየሱስ ቤተክርስቲያን የሚከበረው የደብረታቦር በዓል በናፍቆት ይጠበቃል፡፡ የብዙዎችን ቀልብም ይስባል፡፡

የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የባሕል እሴቶች እና ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ ሄኖክ ተካ ደብረ ታቦርን በደብረታቦር በታላቅ ድምቀት የሚከበር በዓል መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በዓሉ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ እንደሚከበርም ገልጸዋል፡፡ በዓሉን ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ይዘቱን እንደጠበቀ በድምቀት ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

ደብረ ታቦርን በደብረታቦር በዓል በኢየሱስ ቤተክርስቲያን ታቦታት ወጥተው፣ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ተጠብቆ፣ ምዕመናን ተሠባሥበው የሚከበር በዓል መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ከቤተክርስቲያኗ ጋር በጋራ እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ ከሃይማኖታዊ በዓሉ በተጨማሪ ባሕላዊ ክዋኔዎች እንደሚኖሩም ተናግረዋል፡፡

የቡሔ ባሕላዊ ዜማዎች፣ ክዋኔዎች እና የልጃገረዶች የአሸንድየ ጨዋታዎች ይኖራሉ ነው ያሉት፡፡ በዓሉን የተመለከተ አውደ ጥናት እንደሚኖር የተናገሩት ቡድን መሪው ከደብረ ታቦር ዪኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚኖርም ተናግረዋል፡፡ ሕዝባዊ እና ሃይማኖታዊ በዓል በመኾኑ ሕዝቡ በድምቀት እንደሚያከብረውም ገልጸዋል፡፡ የደብረ ታቦር ከተማ መገለጫ የኾኑ ደብረ ታቦርን በደብረታቦር እና የቅዱስ መርቆሪዎስ በዓላት ዓለም አቀፍ በዓላት እንዲኾኑ በማሰብ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል፡፡

ከሁለቱ በዓላት ባለፈ ሌሎች በዓላትን የማስተዋወቅ እና የማልማት ሥራ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ የሚያራዝሙ ሥራዎች ወደፊት እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡ የቱሪዝም ሃብቶችን የማስፋት እና የማልማት ሥራ በትኩረት ይሠራበታልም ብለዋል፡፡ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ሁሉም ለሰላም እንዲሠራም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ከሀገር ውጭም ይሁን ከሀገር ውስጥ ያለ ሕዝብ በዓሉን ደብረታቦር ተገኝቶ እንዲያከብርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደሴ ከተማ ከ21ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የተለያዩ የልማት ሥራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።
Next articleበየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ሥራ አሥፈፃሚዎች ሥነ ምግባርን በመላበስ በተገቢው መንገድ ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉ ተጠየቀ።