በየዘመናቱ ሳይመለሱ ለቀሩ የሕዝብ ጥያቄዎች መፍትሔ ለመስጠት እና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሀገራዊ ምክክር ወሳኝ ሚና እንዳለው ተገለጸ።

14

ባሕር ዳር: ነሐሴ 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ምክክሩ በአለመግባባት የሚባክን ሃብት እና የሰው ሕይዎትን በመታደግ ዘላቂ ሰላምን የሚያጸና ነው፡፡ ምክክር፣ ድርድር እና ሽምግልና ለዘመናት ላጋጠሙ ችግሮች መፍቻ ቁልፍ ከመኾን አልፈው እንደ ሕግም የሚከበሩ እና የሚተገበሩ ባሕላዊ እሴቶቻችን ኾነው አገልግለዋል።

ሀገራዊ ምክክር ለሀገራችን ኢትዮጵያ አዲስ ልምምድ እንደመኾኑ መጠን ፅንሰ ሃሳቡ ከሌሎች የግጭት አፈታት ሂደቶች ጋር እየተቀላቀለ ብዥታን ሲፈጥር ይስተዋላል፡፡ የምክክር፣ የድርድር እና የሽምግልና ልዩነቶች እንዲሁም አንድነቶች ምንድን ናቸው? ከሌሎች የሰላም ግንባታ ሂደቶች በምን ይለያል?
የእርቀ ሰላም ባለሙያ እና አማካሪ ጋረደው አሰፋ እንደሚሉት ምክክር ማለት የተለያዩ ፍላጎቶች ሲስተዋሉ፣ ልዩነቶች ወደ ተካረረ መንገድ ሲያመሩ፣ ሀገራዊ የኾኑ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ሲያጋጥሙ እና በተደጋጋሚ ወደ ጦርነት የሚያስገቡ ምክንያቶችን በንግግር ለመፍታት እንዲሁም የአቅጣጫ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ የሰላም ሂደት ነው፡፡

ምክክር ዜጎች በአንድ ተቋም ጥላ ስር በመኾን ላጋጠማቸው ችግሮች በጥልቀት ተወያይተው እና ተነጋግረው የመፍትሔ ሃሳብ እንዲያመነጩ የሚረዳ ተመራጭ የሰላም ሂደት እንደኾነ ይገልጻሉ። ምክክር የሚያመጣው ውጤት ሳይኾን በምክክር ውስጥ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ ነገሮችን የሚያመላክት ነው የሚሉት ባለሙያው በምክክር እስካሁን ምላሽ ያላገኙ እና በሕዝብ መካከል መከፋፈል የፈጠሩ ጉዳዮችን መስመር በማስያዝ ቀጣይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አለመግባባቶችን በዘላቂነት ይፈታል ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ድርድር ከጦርነት እና ወደ ጦርነት ከሚወስድ ውዝግብ ለመውጣት የሚደረግ የሰጥቶ መቀበል መርሕን የሚከተል የሰላም ሂደት መኾኑንም ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት እንደ ማሳያ ያነሳሉ፡፡ የድርድር ሂደት በውስጡ ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን እንደሚይዝ የሚገልጹት አቶ ጋረደው የመጀመሪያው ጦርነት በማቆም ወደ ተሻለ ሰላም መመለስ ሲኾን ሌላኛው ዳግም ወደ ጦርነት ላለመግባት ስምምነት ማድረግን ይፈልጋል ይላሉ፡፡

እርቅ (ሽምግልና) ማለት ጦርነት በሌለበት ሁኔታ በታሪክ ሂደቶች፣ በተፈጠሩ ትርክቶች እና በተለያዩ ምክንያቶች ማኅበረሰብ ተኳርፎ ሲቀመጥ እና ወደ አወንታዊ ሰላም ለመመለስ የሚረዳ ድልድይ መኾኑን አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ ባሕል የሚፈቅደው ማስታረቅን እና ወደ ቦታው መመለስን እንደኾነ የሚያስረዱት አቶ ጋረደው እርቅ (ሽምግልና) ሰዎች ከኩርፊያ ወጥተው አብሮ ወደሚኖሩበት ሁኔታ የሚያሸጋግር አፍሪካዊ እንዲሁም ሀገር በቀል ማኅበራዊ የሰላም ሥርዓት መኾኑን ያብራራሉ፡፡

በኢትዮጵያ የሚነሱ የመሬት፣ የሕገ መንግሥት፣ የቋንቋ እና የመሳሰሉ ጉዳዮች ከታች ወደ ላይ እናምጣቸው ቢባል ዕድሜ ልክ በንትርክ ውስጥ ከመቆየቱ የተነሳ መፍትሔ ለማምጣት አዳጋች እንደሚኾን የሚጠቁሙት አቶ ጋረደው ነገር ግን ምክክሩን የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የትምህርት ምሑራን እንዲሁም መገናኛ ብዙኀኖችን ጨምሮ መሰል አካላት አድርገውት ወደ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል እንዲወርድ የሚደረግ ከሞላ ጎደል ፖለቲካዊ የሚመስል የሰላም ሂደት እንደኾነ ይጠቁማሉ።

ኮሚሽኑ የተከተለው አካሄድ ከታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል ወደ ምሑራን መኾኑን አንስተው ይህም ሂደቱን እንዳይፋጠን ሊያደርገው ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ምክክር የብዙ ሰዎችን ተሳትፎ ቢጠይቅም ሁሉንም ሕዝብ ማመካከር በጣም አስቸጋሪ መኾኑን የሚያነሱት የእርቀ ሰላም ባለሙያው ነገር ግን በመጀመሪያ ደረጃ ለተከሰቱ ችግሮች ዋነኛ ተዋናይ የኾኑ አካላት በጉዳዩ ላይ በጥልቀት እንዲመክሩበት ማድረግ ያስፈልጋል ነው የሚሉት፡፡

የኢትዮጵያ የሀገራዊ ምክክርም በዚሁ ሂደት ቢመራ ውጤታማ ሊኾን እንደሚችል የመፍትሔ ሃሳባቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ጠበቃ እና የሕግ ባለሙያ ፍቃዱ ጴጥሮስ ምክክር ማለት በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ስለገጠማቸው የተለያዩ ችግሮች ምን ማድረግ እንዳለባቸው በጋራ የሚነጋገሩበት መድረክ ነው፡፡
ምክክር ከሌሎቹ የሰላም ግንባታ ሂደቶች አንጻር የሁሉም ፍላጎት የሚንጸባረቅበት፣ ብዙ ተሳታፊ እና ረጅም ጊዜ ስለሚወስድ ወደሚፈለገው የጋራ ግብ ለመድረስ የሁሉንም ዜጎች አጀንዳ ማሠባሠብ እንደሚጠይቅ ይገልጻሉ፡፡

ላጋጠሙ ችግሮች ብቻ ለብቻ አስቀምጦ በማነጋገር መፍትሔ ማምጣት ሳይቻል ሲቀር ዜጎች ወደ ምክክር ሥርዓት እንደሚገቡ ይገልጻሉ፡፡ የምክክር ሂደት መግባባት ላይ የተመሠረተ ሲኾን በውስጥ የሚከናወኑ ተግባራት ግልጽ በኾነ መንገድ ይቀመጣል፣ የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ ይኖረዋል፣ በስተመጨረሻ ውጤቱም የሕዝብ ተቀባይነትን ያገኛል ነው ያሉት፡፡

ምክክር ሂደቱን ከሚያስተባብሩ እና ከሚያመቻቹ አካላት ውጪ ሌላ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት የለበትም ይላሉ፡፡ በምክክር ሂደት ላይ አብዛኛው ነገር የጋራ መኾኑን የሚገልጹት አቶ ፍቃዱ በመጀመሪያ ምክክር የሚፈልጉትን ነገሮች ግልጽ አድርጎ ማስቀመጥ እና መለየት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

ምክክር ትኩረቱ ሰቶ መቀበል ላይ ሳይኾን በሀገር አቀፍ ደረጃ የጋራ መግባባት እና ሰላም መፍጠር መኾኑን ጠቅሰው ዋና ባሕሪው የጋራ መግባባት ለመፍጠር እንዴት እንሂድ የሚል ነው ብለዋል ለኢዜአ በሰጡት ሃሳብ፡፡ ድርድር ሲኾን ይህም ሰቶ መቀበል ላይ የተመሠረተ በመኾኑ እያንዳንዱ አካል አስቀድሞ ምን እንደሚቀበል እና ምን እንደሚሰጥ ይታወቃል ብለዋል፡፡

ሂደቱ ከሞላ ጎደል ግልጽ ላይኾን ይችላል የሚሉት የሕግ ባለሙያው በሂደቱ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡ በምክክር እና በድርድር ውስጥ ጉዳዩን አድምጦ ውሳኔ የሚሰጥ አካል እንደማይኖርም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ሽምግልና (እርቅ) ማለት በመቀያየም ወይም ባለመግባባት ውስጥ ያሉ ወገኖች ሃሳባቸውን ካቀረቡ በኋላ አሸማጋዮች በሚሰጡት የእርቅ ሃሳብ የነበሩ ችግሮች እንደሚፈቱ ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኀብረተሰቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን የመልማት እና በተገቢው መንገድ የመገልገል መብቱን ልናረጋግጥ ይገባል” ኢብራሂም መሐመድ (ዶ.ር)
Next articleበደሴ ከተማ ከ21ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው የተለያዩ የልማት ሥራዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ።