
ጎንደር: ነሐሴ 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አስተዳደር የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን እየገመገመ ነው። በግምገማ መድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ኢብራሂም መሐመድ (ዶ.ር) በ2016 በጀት ዓመት ክልሉ የገጠመው ፈተና አሁን ከተገኘው ውጤት በላይ እንዳይሠራ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ በሰላም እና ልማት የመጡትን መሻሻሎች ማስቀጠል እንደሚገባ አንስተዋል። ኀላፊው አክለውም ኅብረተሰቡ በየመድረኩ “በርካታ አገልግሎቶች በእጅ መንሻ መኾናቸውን እየነገረን ነው” ብለዋል። ይኽ መለወጥ እንዳለበት አንስተዋል። “ሕዝቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸውን የመልማት እና በተገቢው መንገድ የመገልገል መብቱን ልናረጋግጥ” ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ በበኩላቸው ሕዝቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ለመፍታት እና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የተለያዩ አሠራሮች መዘርጋታቸውን አንስተዋል። ለአብነት የከንቲባ፣ የሥራ አስኪያጅ እና የሥራ አስፈጻሚ ችሎቶች ሕዝቡን ከመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋር በቀጥታ በማገናኘት በርካታ ጉዳዮች መፍትሔ እንዲያገኙ ማስቻላቸውን ተናግረዋል።
በመድረኩ የመምሪያ ኀላፊዎች፣ የልማት ድርጅቶች፣ የክፍለ ከተማ እና የቀበሌ አመራሮች እየተሳተፉ ሲኾን ውይይቱ መልካም ሥራዎችን ለማስቀጠል እና ችግሮቹን ለመፍታት እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።
ዘጋቢ፦ አገኘሁ አበባው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!