
ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ ቱመሮ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ግንባታን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) በተገኙበት ዛሬ መጀመሩ ተገልጿል። በ35 ሄክታር መሬት ላይ ከቻይናው CCCC ጋር በአጋርነት የሚገነባው የአዲስ ቱሞሮ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በከተማ ውስጥ አዲስ ከተማን የመገንባት ያህል ግዙፍ ፕሮጀክት መኾኑ ተገልጿል።
ፕሮጄክቱ በውስጡ ትላልቅ ሞሎችን፣ የመኖሪያ አፓርትመንቶችን፣ ቢሮዎችን፣ የትምህርት ተቋማትን፣ የጤና ተቋማትን እንዲሁም ሰፋፊ የመዝናኛና የውኃ አካላትን፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላትን ያካተተ መሆኑ ተመላክቷል። ይህ የአዲስ ቱሞሮ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ለአዲስ አበባ አዲስ ገፅታ የሚያላብስ፣ ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነቷን የሚያጎላ፣ ተጨማሪ የውበት ምንጭ የሚሆን፣ ለነዋሪዎች ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጥር፣ ንግድን የሚያሳልጥ፣ ትልቅ ዓለም አቀፍ የግብይት ማዕከል እንደሚኾንም ተጠቅሷል።
ማኅበራዊ አገልግሎቶች የሚሰጡ መሰረተ ልማቶችን ያካተተ መኾኑንና በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!