6 ነጥብ 9 ሚሊየን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ማቀዱን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

67

ባሕር ዳር: ነሐሴ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2017 የትምህርት ዘመን 6 ነጥብ 9 ሚሊየን ተማሪዎችን ለመመዝገብ አቅዶ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡ በክልሉ ባለፉት አምስት ዓመታት ተከታታይ የትምህርት ተሳትፎ ውስንነት ተስተውሏል ብለዋል የአማራ ክልል ትምህር ቢሮ ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጌታቸው ቢያዝን። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች እንዲሁም በክልሉ ባለፈው አንድ ዓመት የዘለቀው ግጭት የትምህርት ተሳትፎው ውስንነት ዓበይት ምክንያቶች እንደነበሩ አንስተዋል፡፡

በተለይም በክልሉ ባለፈው አንድ ዓመት የዘለቀው የሰላም እጦት በትምህርት ዘርፉ ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ የጎላ ነበር ተብሏል፡፡ በ2016 የትምህርት ዘመን ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ነበሩ ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ከ3 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶችም ሙሉ በሙሉ ተዘግተው መክረማቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት የትምህርት ዘመን አንጻራዊ ሰላም ባገኙ አካባቢዎች የመማር ማስተማሩን ሥራ ከማስቀጠል ባለፈ የማካካሻ ትምህርት መርሐ ግብሮችን በማዘጋጀት የ6ኛ፣ 8ኛ እና 12ኛ ክፍሎች ክልል አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎችን ለመስጠት መቻሉን አቶ ጌታቸው ጠቁመዋል፡፡ ምንም እንኳን የመማር ማስተማር ሥራው በበርካታ አካባቢዎች እና ትምህርት ቤቶች ቢቋረጥም በችግር ውስጥ ተሁኖም ከ14 ሚሊየን በላይ መጽሐፍትን አሳትሞ ለትምህርት ቤቶች ማሰራጨት መቻሉንም አንስተዋል፡፡

“በ2016 የትምህርት ዘመን የነበሩ የትምህርቱ ዘርፍ ችግሮች በ2017 የትምህርት ዘመን አብረውን እንዲሻገሩን አንሻም” ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እቅድ ተዘጋጅቶ በየደረጃው ከሚገኘው የትምህርት ባለድርሻ ጋር የጋራ መግባባት በመፍጠር አፈጻጸሙ እስከ ወረዳ ድረስ ወርዷል ብለዋል፡፡

የቅድመ ዝግጅት እቅዱ ሁለት መሠረታዊ ዓላማዎች አሉት ያሉት አቶ ጌታቸው በየትምህርት ቤቶቹ የትምህርት መሠረተ ልማትን ማሟላት እና የተማሪዎችን ምዝገባ ቀድሞ ጀምሮ ቀድሞ ማጠናቀቅ ናቸው ብለዋል፡፡ የ2017 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ነሐሴ 20/2016 ዓ.ም ተጀምሮ ጳጉሜ ላይ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በተማሪዎች ምዝገባ ባለፈው ዓመት ያቋረጡ፣ አዲስ ተመዝጋቢዎች እና የነባር ተማሪዎች ምዝገባ ትኩረት ተሰጥቶታል ተብሏል፡፡ በትምህርት ዘመኑ 6 ነጥብ 9 ሚሊየን ተማሪዎችን ለመመዝገብ መታቀዱንም አቶ ጌታቸው ቢያዝን ተናግረዋል፡፡ የክረምት ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ስኬታማ እንዲኾኑ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ የሲቪክ ማኅበራት እና ማኅበረሰቡ ድጋፍ የጎላ ነውም ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የግብርናችንን እምቅ አቅም እና ጸጋ እንጠቀም” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ
Next articleየኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማኅበር የዘንድሮ ማዳበሪያ ማጓጓዝ ሥራ ማጠናቀቁን አስታወቀ።