
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 29/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዳንግላ ነዋሪው መምህር በላይነህ እንዳለው ከልጆቻቸውና ባለቤታቸው ጋር በመመካከር ባለ 13 ክፍል ዘመናዊ ቤት ለኮሮና ወረርሽኝ ለይቶ ማቆያና ክትትል ማድረጊያ እንዲያገለግል መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
መምህር በላይነህ ለአብመድ እንደተናገሩት 13 ክፍል ያለውና ገና ለአግልገሎት ያላዋሉት አዲስ ቤት ነው፡፡ የለገሱት ቤት የኮሮና ወረረሽኝ መፍትሔ እስከሚያገኝ ድረስ ለአግልግሎት እንደሚውልም አስታውቀዋል፡፡ ግምባታው እንደጠተናቀቀ አንድም ቀን ለራሳቸው ጥቅም ሳያውሉ ለኮሮና መከላከል እንዳቀረቡ ተናግረዋል፡፡ ባለ 13 ክፍል ቤት ከሆስፒታሉ አጠገብ የሚገኝ በመሆኑ ለግብረ ኃይሉ እና ጤና ባለሙያዎች በቅርበት ሆነው አግልግሎት እንዲሰጡም ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር መምህር በላይነህ ተናግረዋል፡፡
በዳንግላ ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና የተጉዱ ወገኖችን ለመረዳት የተቋቋመው ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል እና የወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ካሳሁን እማኛው በወረዳው በኮሮኛ ወረረሽኝ ምክንያት የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፈሎች እንዳይጎዱ የገቢ አሰባሰብ መረሀ ግብር ተዘጋጅቶ ልዩ ልዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
እስካሁን ከ251 ሺህ ብር በላይ በካሽ፣ በዓይነት ደግሞ 50 ኩንታል በቆሎ፣ 240 ደርዘን ውኃ፣ 2ሺህ 500 ዳቦ እና እን ለሕሙማን ማቆያ የሚያገለግል 13 ክፍል የተሟላ ሻወር እና ሽንት ቤት ያሉት ዘመናዊ ቤት መገኘቱን አቶ ካሳሁን አስታውቀዋል፡፡
እንደመምህር በላይነህ ያሉት ግለሰቦች የግል ቤታቸውን ለግብረ ኃይሉ ማስረከባቸውን የተናገሩት አቶ ካሳሁን በሌሎች አካባቢዎች እንደሚደረገው የዳንግላ ወረዳ ባለሀብቶችም የግል መኪኖችን ለግብረ ኃይሉ ቢለግሱ የተሻለ መሥራት እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ፎቶ፡- በካሳሁን እማኛው