
ባሕር ዳር: ነሐሴ 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ወይዘሮ አትጠገብ መኳንንት ይባላሉ፤ አራት ልጆችን ወልደው ያሳደጉ እናት ናቸው፡፡ የመኖሪያ ቀያቸው በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ ወይብላ ማርያም ነው፡፡ ልጆቻቸው ለደቂቃም እንዳይለየዩቸው አድርገው እንዳሳደጓቸው ይናገራሉ፡፡ ልጆቻቸው ከአንዱ በስተቀር በሚገባ እስከ አራት ዓመት ድረስ የእናት ጡት ጠብተው ያደጉ ስለመኾናቸው ነው የነገሩን፡፡
ለመኾኑ እኝህ ገራገር እናት አንደኛው ልጃቸው ለምን ጡት ሳይጠባ አደገ? ወይዘሮ አትጠገብ መኳንንት የነበረውን ኹኔታ እንዲህ ያስታውሱታል፡፡ በሀገሬው ባሕል እና ወግ ልጅህን ለልጄ ማለት ያለም የነበረም ነው፡፡ ያኔ እንደ አሁኑ የሚፈጠረውን ችግር የሚያስረዳ ባልነበረበት ጊዜ ወላጆቻቸው ወግ ማዕረግ ለማየት ሲሉ በአንቀልባ ለባል እንደሰጡአቸው እና ‘ግጥግጥ’ የሚሉትን ሥርዓት አካሂደው እንደ ዳሯቸው ነግረውናል፡፡
ወይዘሮ አትጠገብ መኳንንት ሁኔታውን ሲያስታውሱ ያኔ በሕጻንነት ይዳሩ እንጂ ወደ ጎጆ ያመሩት ከ16 ዓመት በኋላ እንደነበር ነግረውን በቀጭኑ የስልክ መስመር ሁኔታውን አስታውሰው ረጅም ሳቅ ሳቁ፡፡ ወይዘሮ አትጠገብ መኳንንት ትዝታቸውን ቀጥለዋል፤ በእኛ ሀገር ባል ክቡር ነው ዕድሜ በቂ ባይኾንም ጡትም በሚገባው ብቅ ብቅ ባይልም ወደ ትዳር ተገባ ይላሉ፡፡
ወዲያው ግን ማርገዝ እና መውለድ ተከተለ ካሉ በኃላ ልጁ ሲመጣ ጡት ማጥባት አልተቻለም ብለው አሁንም ሳቁ፡፡ ኹኔታው አስቸጋሪ ነበር፤ ጡቱ ከልጅነት ይሁን ከሌላ ኹኔታ ወተት እንቢ አለ፤ ልጃቸውም ባሏቸው ጥገቶች ወተት አደገ ብለዋል፡፡ ወይዘሮ አትጠገብ መኳንንት አሁን ላይ ሌሎች ልጆቻቸው በሚገባ ጡት ጠብተው ቢያድጉም የጡትን ጠቀሜታ ሲረዱ የመጀመሪያ ልጃቸው ጡት ጠብቶ ባለማደጉ ውስጣቸውን እንደሚከነክነው ነው የነገሩን፡፡
በጥበበ ጊዮን ሆስፒታል የሕጻናት ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር በለጠ ሰዋሰው እንደነገሩን የእናት ጡት በተፈጥሮው የተሟላ እና የተመጣጠነ ነው፡፡ የእናት ጡት ለተወሰነ የዕድሜ ክልል ሁሉንም ነገር የያዘ እና የተመጣጠነ ንጥረ ነገር በውስጡ የያዘ በመኾኑ ሕጻናት ሁለት ዓመት እስኪሞላቸው የእናት ጡት ወተት መጥባት እንደሚኖርባቸው ነው ዶክተሩ የሚያብራሩት፡፡
✍️ የእናት ጡት ወተት በውስጡ ምን ምን ይዟል?
የእናት ጡት ወተት በውስጡ የያዛቸውን ንጥረ ነገሮች ስንመለከት ለሰውነት ግንባታ አገልግሎት የሚውሉ ካርቦኃይድሬት፣ ፕሮቲን፣ በሽታ ተከላካይ ንጥረ ነገሮችን በበቂ ኹኔታ የያዘ ነው ይላሉ ዶክተር በለጠ፡፡ ልጆች ዕድገታቸው የተሰተካከለ እንዲኾን እና አንድ ሰው በተፈጥሮው ሊያልፍባቸው የሚገቡ ሂደቶችን በትክክል እንዲያልፍ ሊያደርግ የሚችል እንደኾነም ያስረዳሉ፡፡
በሰውነት ሊከሰት የሚችልን ህመም ከመቀነስ እና ሰውነትን ከመገንባትም በላይ በዕድገቱ ውስጥ ላለው የአዕምሮ ንቃቱ አስፈላጊ የሚባሉ ንጥረ ምግቦችን የያዘ ነው ብለዋል፡፡ አንድ ልጅ የተለየ ምክንያት ኖሮ ጡት እንዳይጠባ በሐኪሞች እስካልታዘዘ ድረስ በተወለደ በአንድ ሰዓት ውስጥ ጡት መጥባት እንደሚገባውም ዶክተር በለጠ ተናግረዋል፡፡
በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ሌላ ተጨማሪ ነገር ሳያስፈልገው ጡት ብቻ መጥባት እንደሚኖርበትም ነው ያስገነዘቡት፡፡ የዓለም ጤና ድርጅትን መረጃን ጠቅሰው ዶክተር በለጠ እንደሚሉት በመጀመሪያው ስድስት ወራት ውስጥ ውኃም ቢኾን መስጠት ተገቢ አይደለም፡፡ እናቶች በአስቸጋሪ ጊዜም ቢኾን ልጆቻቸውን ማጥባት እንዳለባቸው የሚናገሩት ዶክተር በለጠ ኅብረተሰቡ እየደገፋቸው ለቀጣይ የተስተካከለ ትውልድ ሲባል ልጆች ጡት መጥባት እንደሚኖርባቸው ነው የሚገልጹት፡፡ በተለይም በሰው ሠራሽም ይሁን በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት በመጠለያ ላይ ያሉ እናቶች ልጆቻቸውን ጡት ማጥባት እንዲችሉ እገዛ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
✍️ ጡት ማጥባት በኢትዮጵያ፡-
በኢትዮጵያ ጡት ማጥባት ኅብረተሰቡ ጥቅሙን አውቆት ለዚህ ሥራ ተገቢውን ትኩረት ባይሰጥም እናቶች በተለምዶ ጡት እንደሚያጠቡ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጅ በበቂ ኹኔታ እናቶች ልጆቻቸው ጡት እንዲጠቡ እያደረጉ እንዳልኾነ አብራርተዋል፡፡ የኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት በ2023 የምግብ እና ሥርዓተ ምግብ ጥናት እንደ ሀገር 77 በመቶ የሚኾኑ እናቶች በወለዱ በአንድ ሰዓት ውስጥ እያጠቡ እንደኾነ እና እንደ አማራ ክልል 75 በመቶ እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡ እናቶች እስከ ስድስት ወር ጡት በማጥባት በኩል እንደ ሀገር 61 በመቶ እንደሚያሳይ እና እንደ አማራ ክልል ደግሞ 73 በመቶ እንደኾነ ገልጸው ይህን የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል እና ከፍ ማድረግ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡
✍️ ጡት ባለመጥባት ምክንያት በሀገር ደረጃ ምን ጉዳት አስከተለ?
ዶክተር በለጠ ሰዋሰው እንደሚሉት ሕጻናት በበቂ ኹኔታ እና ሳይንሱ በሚያዘው መሠረት ባለመጥባታቸው የመቀንጨር ኹኔታ ስለመከሰቱ አብራርተዋል፡፡ በተለይም እንደ ሀገር የዚሁ ችግር 39 በመቶ የሚኾኑ ሕጻናት መቀንጨር እንዲከሰት ስለማድረጉ እና በክልሉ ደረጃ ደግሞ 40 በመቶ ሕጻናት መቀንጨር እንዲከሰትባቸው እንዳደረገ ገልጸዋል። ይህን ለመከላከል እስከ ሁለት ዓመት የእናት ጡት ወሳኝ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡ የእናት ጡት ማጥባት ላይ በሦስት ደረጃዎች ከፍሎ መሥራት እንደሚገባም ዶክተር በለጠ ሰዋሰው ይመክራሉ፡፡
✍️ 270 ቀን ከጸነሰች እስከምትወልድ ድረስ ያለው እንደኛው ነው፡፡
✍️ እስከ ስድስት ወር ያለው 180 ቀን ደግሞ ሌላኛው ነው
✍️ ከስድስት ወር እስከ ሁለት ዓመት ድረስ 550 ቀን በአጠቃላይ 1 ሺህ ቀናት ላይ መሠራት እንዳለበት እና ለዚህም ሁሉም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባው መክረዋል፡፡ በሀገር ደረጃ የወደፊቱ ሀገር ተረካቢ ዜጋ ከሌላው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ እንዲኾን እና ለሀገር አሳቢ ዜጋ እንዲፈጠር ካስፈለገ ሕጻናት በወቅቱ የእናት ጡት ወተት በበቂ አግኝተው እንዲያድጉ ማድረግ እንዳለባቸውም ዶክተር በለጠ መክረዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!