
ባሕር ዳር: ነሐሴ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመላክተዉ አጠቃላይ ከሀገሪቱ የመሬት ሽፋን 74 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር የሚኾነዉ ለግብርና ተስማሚ ነዉ፡፡ ይህም ሀገሪቱን ለሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንት ምቹ ያደርጋታል፡፡ በሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ የሚመረቱ ምርቶች ከዉጭ የሚገቡትን በሀገር ዉስጥ ምርቶች ከመተካታቸዉ ባሻገር ለዉጭ ምንዛሬ ገቢ ከፍተኛ ሚናን ይጫዎታሉ፡፡ለዚህ ደግሞ የቅባት እህሎች ዋቢ እና ማሳያ ናቸዉ፡፡
በአማራ ክልል ለእርሻ ኢንቨስትመንት ምቹ ከኾኑ አካባቢዎች ዉስጥ የምዕራባ ጎንደር ተጠቃሽ ነዉ፡፡ በዞኑ ከ900 በላይ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች መኖራቸዉን የዞኑ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ መሰንበት መልካሙ አስታዉቀዋል፡፡ ባለሃብቶች ከ101 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ተቀብለዉ የተለያዩ ለዉጭ ገበያ የሚዉሉ ምርቶችን እንደሚያመርቱም ተናግረዋል፡፡
የምዕራብ ጎንደር ዞን ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚኾኑ ምርቶችን በማምረት በኩልም የተሻለ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ዞን ነው። ይህንን ምቹ ኹኔታ በመጠቀም በስፋት ባለሀብቶች ለልማት እንዲሰማሩ በተለያዩ ሚዲያዎች፣ በአካል በማወያየት እና በኢትዮጵያ ታምርት የንቅናቄ መድረክ በመፍጠር የማስተዋወቅ ሥራዎች ይሠራል ብለዋል የዞኑ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ መሰንበት መልካሙ ።
ክልሉ በተፈጥሮ የታደለ ነዉ፤ የአየር ንብረቱ፣ የአፈር ኹኔታዉ፣ የዉኃ አቅርቦቱም በአጠቃላይ ለእርሻ ኢንቨስትመንት ምቹ ነዉ ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ ናቸው። በተለይ ገበያ ተኮር የኾኑ ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ለኤክስፖርትም ኾነ ተኪ ምርት በማምረትም ለኢኮኖሚዉ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተሠራባቸው ይገኛሉ ብለዋል ፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!