
ደብረ ማርቆስ: ነሐሴ 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባለፈው ዓመት የተከሰተው የሰላም መደፍረስ ችግር ካስከተለው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ባሻገር የሕዝቡ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች እንዳይፈቱ ከፍተኛ መስተጓጎል ማስከተሉ ይታወሳል። የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ ባለፈው ዓመት በግጭት ምክንያት ሕዝቡ ያጣውን ልማት ለማካካስ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ ደግሞ በዞኑ በየደረጃው የሚገኙ መሪዎች እና ባለሙያዎች ኀላፊነት ከፍተኛ ሊኾን ይገባል ነው ያሉት። አቶ ኑርልኝ የታቀዱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች እንዲሳኩ እና ችግሮች እንዲታረሙ ግብዓቶች በመስጠት እና አጥፊዎችን በመገሰጽ የዞኑ ሕዝብ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በዞኑ የሚገኙ የሥራ ኀላፊዎችም የሕዝባቸውን የልማት እና የመልካም አሥተዳር ችግሮች ለመፍታት በተያዘው በጀት ዓመት በትኩረት እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። የደጀን ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ይርጋ በዛ እና የእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ወንዲፍራው ጀመረ በተያዘው በጀት ዓመት ሕዝቡን በማስተባበር ባለፈው ዓመት የተስተጓጎሉ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ተግባራትን ለማካካስ አየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባለፈው በጀት ዓመት የነበሩ አፈፃፀሞችን በመገምገም በተያዘው ዓመት የታቀዱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ግቦችን ማሳካት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ያለሙ ዞናዊ የውይይት መድረክ በደጀን ከተማ እየተካሄደ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!