“የህወሓት ድርጊት የትግራይ ሕዝብ ያገኘውን አንጻራዊ ሰላም እንደመንጠቅ ይቆጠራል” ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር)

31

ባሕር ዳር: ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሉት “በየትኛውም የዓለም ጥግ ያለ ሀገር የሚመራው በሕግ እና በሥርዓት ነው፤ ሕግ እና ሥርዓት ከማንኛውም ሰው፣ ተቋም፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ ቡድን እና ሥብሥብ በላይ ነው” ብለዋል፡፡

የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ሕግ እና ሥርዓትን አክብሮ የማይንቀሳቀስ የትኛውም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ የመጨረሻ ግቡ ጥፋት እንደኾነም አስረድተዋል። የህወሓት ያለፉት ዓመታት የግትርነት ባህሪም የዚሁ ምሳሌ እንደኾነ ነው ያስገነዘቡት። ህወሓት ደጋግሞ እንደመሸሸጊያ የሚያነሳው የፕሪቶሪያ ስምምነትም ቢኾን የፌዴራል ተቋማትን አሠራሮች፣ ሕጎች እና አካሄዶች በጥብቅ እንዲያከብር ግዴታ እንደጣለበትም ነው ያብራሩት።

ቀድሞ የገባውን ግዴታ ሲሸራርፍ የመጣው ህወሓት ዛሬ በተጨባጭ ተግባር ስምምነቱን ደምስሶታል ብለዋል፡፡ ድርጊቱ የትግራይ ሕዝብ ያገኘውን አንጻራዊ ሰላም እንደመንጠቅ ይቆጠራል፤ ስህተት መሥራት ያለ እና የሚጠበቅ ነው፤ በተመሳሳይ መንገድ ተመሳሳይ ስህተት መፈጸም ግን የመጨረሻው የጥፋት መንገድ ነው ሲሉ ነው ያብራሩት፡፡

አሁን ላይ እየተፈጸመ ላለው ስህተት ደግሞ ብቸኛው ተጠያቂ እራሱ ህወሓት እንደኾነም አስረድተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየክልል ከተሞች እርስ በእርሳቸው በአየር ትራንስፖርት እንዲገናኙ እየሠራ መኾኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገለጸ።
Next articleችግሮች እንዲታረሙ ግብዓቶችን በመስጠት እና አጥፊዎችን በመገሰጽ ሕዝቡ የድርሻውን እንዲወጣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ አሳሰቡ።