
ባሕር ዳር: ነሐሴ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የክልል ከተሞች እርስ በርሳቸው እንዲገናኙ የማድረግ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ከማስፋት ባሻገር የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን ማስፋት ላይም ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው።
አየር መንገዱ ከአዲስ አበባ ወደ ክልል ከተሞች መዳረሻዎችን ከማስፋት በተጨማሪ ጥናትን መሰረት በማድረግ የክልል ከተሞችን በአየር ትራንስፖርት የማሥተሳሰር ሥራ እያከናወነ መኾኑን ገልጸዋል። በቅርቡ አየር መንገዱ ባሕር ዳርን ከደሴ እና ኮምቦልቻ፣ ጅግጅጋን ከጎዴ፣ መቀሌን ከሽረ እንዲሁም ጋምቤላን ከአሶሳ በአየር ትራንስፖርት እርስ በእርሳቸው እንዲተሳሰሩ ማድረግ መቻሉን ነው ያስረዱት።
የደብረ ማርቆስ ኤርፖርት ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ከባሕር ዳር ጋር የማገናኘት ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል። የሀገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት ትስስር መጠናከር ለንግድ፣ ለቱሪዝም እና ለኢንቨስትመንት ሥራ መጠናከር አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የክልል ከተሞችን በአየር ትራንስፖርት እርስ በእርሳቸው የማስተሳሰር ሥራ በቀጣይ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። እንደ ኢዜአ ዘገባ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በአሁኑ ወቅት 139 ዓለም አቀፍ እንዲሁም 22 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች አሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!