
ባሕር ዳር: ነሐሴ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገሪቱ የግብርና ኢንቨስትመንት ዕድሎች ጎልተው የሚታዩበት የኢትዮጵያ ግብርና ኢንቨስትመንት ፎረምን ምክንያት በማድረግ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ.ር ) ከዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ልዑካን ቡድን ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ግብርና ሚኒስቴር የተለያዩ መርሐ-ግብሮችን ቀርጾ በአግባቡ በመተግበር ውጤታማ ኾኗል ያሉት ሚኒስትሩ፣ በተለይ በአረንጓዴ አሻራ፣ በመስኖ ስንዴ ልማት እና በሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብሮች የተሻለ ውጤት መመዝገቡን አብራርተዋል። በተገኙት ምርጥ ተሞክሮዎች ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ከኢትዮጵያ ልምድ መቅሰማቸውን ገልጸዋል፡፡
የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ረጅም እድሜ ያስቆጠረ አጋር የልማት ድርጅት መኾኑን ያነሱት ሚኒስትሩ ግብርና ሚኒስቴር በተለያዩ የግብርና ዘርፎች ባስመዘገባቸው ውጤቶች ውስጥም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ከግብርና ሚኒስትር ማኀበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ እና እርሻ ድርጅት ዋና የኢኮኖሚ አማካሪ ማክሲሞ ቶሬሮ (ዶ.ር) በበኩላቸው “ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ያስመዘገበችው ውጤት ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት ነው” ብለዋል። በውጤቱም መደሰታቸውን የገለጹት ማክሲሞ ቶሬሮ (ዶ.ር) ድጋፉም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!