
ባሕር ዳር: ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የቤተ መንግሥቱ የጥገና ሥራ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ ቱሪስቶችን ማስተናገድ እንዲችል የክልሉ መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ። መንግሥት ታሪካዊ ቅርሶችን ጠብቆ ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ ለቅርሶች ጥበቃ እና ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደኾነ ርእሰ መሥተዳድሩ አንስተዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ቅርስ የኾነው የአጼ ፋሲል አብያተ መንግሥት ጥንታዊ እና ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መንገድ እየተሠራ መኾኑንም ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ጠቁመዋል። የጎንደር አብያተ መንግሥታት የዘመኑን መሪዎች የሃሳብ ልዕልና እና ከፍታን የሚያመለክት፤ የዛሬ እና የትናንት ትውልድን የታሪክ አሻራ የሚያስተሳስር ታላቅ የኪነ ሕንጻ ጥበብ ውጤት እና መገለጫ መኾኑንም አስረድተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አመራር ሰጭነት የተጀመረው የቤተ መንግሥቱ የጥገና ሥራ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ ቱሪስቶችን ማስተናገድ እንዲችል የክልሉ መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋልም ነው ያሉት። መንግሥት ታሪካዊ ቅርሶችን ጠብቆ ለመጭው ትውልድ በማስተላለፍ ለቅርሶች ጥበቃ እና ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።
በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ ያሉት የአዘዞ ጎንደር የአስፋልት መንገድ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎች በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኙም መመልከታቸውን ርእሰ መሥተዳድሩ አስገንዝበዋል። የከተማው ነዋሪ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ክልሉ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ርእሰ መሥተዳድሩ የከተማው ሕዝብ ትብብር እና ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ሰላም ለልማት እና ለመልካም አሥተዳደር መሠረት መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ለስላም ኅብረተሰቡ የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል። ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች የልማት ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ እንደኾነ እና የፀጥታ ችግር ባለባቸው ግን የተጀመሩ ፕሮጀክቶች መቆማቸውን ነው ያስገነዘቡት።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ የፌዴራል፣ የክልል እና የከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች ፕሮጀክቶችን በቅርበት እየተከታተሉ መኾኑን ገልጸዋል። የከተማው ነዋሪ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እያደረገ ያለው ትብብር እና ተሳትፎ አበረታች መኾኑንም ነው ያስረዱት።
በከተማው በፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የሕዝቡን የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች የሚፈቱ ናቸው ነው ያሉት። በየደረጃው ያሉ መሪዎች የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ እያደረጉት ያለው ድጋፍ እና ክትትልም ለፕሮጀክቶቹ መፋጠን የጎላ ፋይዳ እንዳለው ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል።
በጉብኝቱ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይን ጨምሮ የከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች መሳተፋቸውን የጎንደር ከተማ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!