
አዲስ አበባ: ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሴቶችን እና ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
በመላ ሀገሪቱ የሚፈፀሙ ጥቃቶች፣ የመብት ጥሰቶች እና የኢኮኖሚ መገለሎችን ለመከላከል ከሚኒስቴሩ ጋር አብረው እንደሚሠሩ በተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ቢሮ ኀላፊ ማርሴል ክዋሚ ተናግረዋል።
የጋራ ሰነዱ የሴቶችን መብት ለማስከበር፣ በጸጥታ ችግር ምክንያት ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን መብት ለማክበር እና ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል፡፡
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋየ (ዶ.ር) የሦስት ዓመት የመግባቢያ እና የትብብር ሰነዱ በተፈጥሮ አደጋ፣ በሰላም እጦት እና በአለመረጋጋት የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በአግባቡ ለማገዝ እንደሚረዳ ነው ያስረዱት።
የጋራ ሰነዱ ተፈርሞ ብቻ የሚቀመጥ ሳይኾን በተግባር በኢትዮጵያውያን ሕይዎት ላይ ተገቢውን ለውጥ በሚያመጣ መልኩ የሚሠራ ነው ብለዋል። ተጨባጭ ሥራ በተግባር እንደሚሠራም አብራርተዋል።
“ኢትዮጵያውያን መሠረታዊ መብቶች መከበር እና የተሻለ ኑሮም ይገባቸዋል፤ እሱን ለማድረግም እናግዛለን” ብለዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!