
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 29/2012 ዓ.ም (አብመድ) ባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የኮሮና ወረርሽኝን ስርጭትን ለመቀነስ ዛሬ በአውራ ጎዳናወቿ የፀረ ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት ማድረግ ጀምራለች። ከረፋዱ 3፡00 ገደማ ጀምሮ ከፓፒረስ ፊት ለፊት ከሚገኘው አደባባይ አንስቶ በጥበብ ሕንጻ እስከ ሃኒ ጋርደን አደባባይ ያለው የከተማዋ አውራ መንገድ በፀረ ተህዋሲያን ኬሚካል ተረጭቷል።
ርጭቱ በሁሉም የከተማዋ ክፍል እንደሚካሄድ የከተማዋ ከንቲባ ተቀዳሚ ምክትል መሐሪ ታደሰ (ዶክተር) አስታውቀዋል። ከዋና ዋና መንገዶች በተጨማሪ የውስጥ ለውስጥና ሰው በብዛት ያስተናግዱ የነበሩ የገበያ ቦታዎችም የኬሚካል ርጭት ሊካድባው ነው።
ለዚህም ተግባር በቂ የኬሚካል አቅርቦትና ርጭት የሚያካሂዱ ስድስት ተሽከርካሪዎች መዘጋጀታቸው ተነግሯል። የከተማዋ ነዋሪዎች የወረርሽኙን ስርጭት አሳሳቢነት በማጤን መንግሥት ያስተላለፈውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረጋቸው ከንቲባው ምሥጋና አቅርበዋል። ‘‘የኬሚካል ርጭት ተካሂዷል’’ በሚል እሳቤ ነዋሪዎች ከቤት መውጣት እንደለሌባቸውም ዶክተር መሐሪ መልእክት አስተላልፈዋል።
የአማራ ክልል ውኃ መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ ኃላፊና የክልሉ የኮሮና ወረርሽኝ መከላከል የውኃ ግብረ ኃይል አባል ዶክተር ማማሩ አያሌው ደግሞ ወረርሽኙን ለመከላከል አማራጭ ከሆኑ ዘዴዎች መካካል የፀረ ተህዋሲያን ርጭት ማካሄድ አንዱ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። የኮሮና ቫይረስ እንዳለባቸው የተጠረጠሩና የተገኙባቸው ሰዎች የታዩባቸው አካባቢዎች ርጭቱ ሲካሄድ የቆየ መሆኑንም ተናግረዋል። በቀጣይም በአራት የለይቶ የሕክምና ክትትል ማድረጊያዎች፣ በ23 ለበሽታው ተጋላጭ ወረዳዎችና በ5 የክልሉ ዋና ዋና ከተሞች ርጭት የሚካሄድ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ:- ኃይሉ ማሞ