ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላትን ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

50

ባሕር ዳር: ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላትን ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡ ወርሐ ነሐሴ በአማራ ክልል ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት በስፋት ይከበራሉ፡፡ በዋግ ሻደይ፣ በሰሜን ወሎ አሸንድዬ እና ሶለል፣ ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር፣ እንገጫ ነቀላ በምሥራቅ ጎጃም በስፋት ይከበራሉ፡፡ እነዚህ በዓላት በሌሎች አካባቢዎችም ይከበራሉ፡፡

በዓላቱ ሃይማኖትን፣ ባሕልን፣ ታሪክን እና እሴትን ይገልጻሉ፡፡ ጥንታዊ ባሕላትን እና በዓላትን በጥንቃቄ የመጠበቅ የሕዝብ ጥበብንም ያሳያሉ፡፡ ወርሐ ነሐሴ ደርሷል፡፡ በዓላቱም የሚከበሩባቸው ቀናት እና ሳምንታት ቀርበዋል፡፡ በናፍቆት የሚጠብቁት የባሕሉ እና የበዓሉ ባለቤቶች ለክብረ በዓሉ ዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዓባይ መንግሥቴ በአማራ ክልል የታሪክ፣ የማንነት መገለጫ፣ የትውልድ ማስተማሪያ የኾኑ፣ ለትውልድም መተላለፍ የሚገባቸው በርካታ የቱሪዝም ሃብቶች አሉ ብለዋል፡፡ ክልሉ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ሃብቶች ባለቤት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የማንነት መገለጫ የኾኑ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት በነሐሴ ወር በስፋት እንደሚከበሩም ገልጸዋል፡፡ በስፋት እና በድምቀት የሚከበሩትን በዓላት ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

በዓላቱ ከአካባቢው አልፈው ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን የሚስቡ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በዓላቱ በድምቀት እየተከበሩ መምጣታቸውን የተናገሩት ምክትል ኀላፊው ለምርምርም ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ነው የተናገሩት፡፡ ዓለም አቀፍ ሃብቶች እንዲኾኑ በማሳብ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ሕዝባዊ በዓላት በመኾናቸው ሕዝቡ በስፋት እንደሚያከብራቸውም አንስተዋል፡፡

በዓላቱ በድምቀት እንዲከበሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ በዓላቱ በክልል ደረጃ በማጠቃለያ ለማክበር እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ በክብረ በዓሉ የበዓላቱ ጥንተ ታሪክ አመጣጥ፣ አሁን ላይ ያሉበትን ደረጃ የሚያሳይ እና ወደፊት በምን መልኩ መጠበቅ እና መተላለፍ አለበት በሚለው ጉዳይ ጥናት እንደሚቀርብም አንስተዋል፡፡

በዓላቱን ጠብቆ ከማስተላለፍ ጎን ለጎን ለሕዝብ ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታ እንዲኖራቸው ለማድረግ ምን መደረግ እንዳለበት የሚያሳይ ጥናት እንደሚቀርብም አመላክተዋል፡፡ ሕዝቡ ለአዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋ የሚያይባቸው ኾነው እንዲከበሩ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ለሥራው ስኬታማነት ደግሞ ግብረ ኀይል ተቋቁሟል ነው ያሉት፡፡ ማኅበረሰቡ በችግር ውስጥም ኾኖ እያከበራቸው የመጡ የማንነቱ መገለጫዎች መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡

ባለፈው በጀት ዓመት በጸጥታ ችግር ውስጥም ኾነው የዕቅዱን 88 በመቶ የሚኾኑ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ክልሉን መጎብኘታቸውንም አስታውሰዋል፡፡ ጎብኝዎቹ የደኅንነት ችግር አልገጠማቸውም ያሉት ምክትል ኀላፊው ማኅበረሰቡ የእንግዳ አቀባበሉ እና አሸኛኘት ባሕሉ ጠንካራ በመኾኑ ችግር እንዳይገጥማቸው ማድረጉን ነው የተናገሩት፡፡

እንደተፈለገው ባይኾንም የውጭ ሀገር ጎብኝዎችም መጎብኘታቸውን ነው የገለጹት፡፡ ጎብኝዎቹ በቅርብ ከሚከበሩት በዓላት መጥተው በበዓላቱ እንዲታደሙ እና እንዲጎበኙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በዓላቱ ባሕላዊ ይዘታቸውን፣ ታሪካቸውን እና ሃይማኖታቸውን ሳይለቁ መከበር እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡ ባሕላዊ ይዘታቸውን ሊበርዝ የሚችል ነገር ሊጨመርበት አይገባምም ብለዋል፡፡ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮም የበዓላቱ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ይዘታቸው ሳይበረዝ እንዲከበሩ በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጎንደር ከተማ ላይ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እየተሠሩ ነው ” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleየደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ የአፈር ለምነትን ለመጨመር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ገለጸ፡፡