
ባሕር ዳር: ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጎንደር ከተማ በፌዴራል እና በክልሉ መንግሥት ትኩረት ተደርጎባቸው እየተሠሩ ያሉ ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ለማየት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ጎንደር ከተማ ገብተዋል።
የአዘዞ አርበኞች አደባባይ 12 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታን ጨምሮ የመገጭ የውኃ ፕሮጀክት፣ የኮሪደር ልማት እና የቤተ መንግሥት ቅርስ ጥገና ሥራ ጉብኝት ተደርጓል። ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የተመለከቷቸው የመንገድ ሥራ እና የፋሲል አብያተ መንግሥት ቅርስ ጥገና ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ሥራቸው እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።
የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት ጎንደር ታሪኳን የሚመጥን ልማት እንዲኖራት እየሠሩ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ለዚህም በጎንደር ከተማ ያለው የተሻለ የሰላም ሁኔታ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም በከተማዋ የተጀመሩ የኮሪደር ልማት፣ የአስፖልት መንገድ እና የቅርስ ጥገና ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ኅብረተሰቡ ሰላሙን አጠናክሮ እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት እንዲጠናቀቁ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አቅጣጫ መሠጠቱ ይታወሳል።
ዘጋቢ፡- ተስፋዬ አይጠገብ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!