“ከእልኸኝነት እና የብሽሽቅ ፖለቲካ መውጣት ይገባል” የፖለቲካ ሳይንስ መምህር

56

ባሕር ዳር: ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ፖለቲካው በዘመመ ቁጥር ሀገር ትዘማለች፡፡ ፖለቲካ ከጠረጴዛ ዙሪያ ሲጠፋ ሀገር ጦር በሚማዘዙ ሰዎች ትሰቃያለች፡፡ ምጣኔ ሃብቷ ይደክማል፣ ማኅበራዊ ግንኙነት ይበጣጠሳል፤ ዜጎች ወጥቶ መግባት፣ ሠርቶ መብላት ብርቅ ይኾንባቸዋል፡፡ ሀገር ሰላም ውላ እንድታድር ሰላማዊ ውይይት፣ ትዕግሥት እና አርቆ አሳቢነት ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዴም ስለ ሀገር ሲባል ችሎ ማለፍ ያሰፈልግ ይኾናል፡፡ ለዚያም ይመስላል አበው “ ሆድ ከሀገር ይስፋል” ሲሉ ብሒል ያስቀመጡት፡፡

ሆድ ሲችል ክፉ ነገሮች ያልፋሉ፤ ሊቀጣጠሉ የነበሩ እሳቶች ይጠፋሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሆድ አልችል ሲል ሀገርን የሚያጎብጥ መከራ ሊወርድ ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ አላባሩ ያሉ ግጭቶች ሲፈትኗት ኖረዋል፤ ዛሬም እየፈተኗት ነው፡፡ አንደኛውን ግጭት ስትሻገር ሌላ ግጭት እየተነሳ ልጆቿን ሲቀጥፍባት፣ ሃብት እና ንብረቷን ሲያወድምባት ኖሯል፡፡ ዛሬም ከዚህ ችግሯ አልተላቀቀችም፡፡ ከጥይት ጩኸት ርቃ በሰላም አድራ አልዋለችም፡፡

በየቀኑ ጥይቶች የሚተኮሱባቸው፣ የተተኮሱ ጥይቶች ሰው ይዘው የሚወድቁባቸው አካባቢዎች ሞልተዋል፡፡ ግጭት ውሎ ካደረባቸው፣ ሞት እና መቁሰል ከሰነበተባቸው አካባቢዎች ደግሞ የአማራ ክልል አንደኛው ነው፡፡ አንድ ዓመት በተሻገረው የአማራ ክልል ግጭት ሰዎች ሞተዋል፤ ንብረት ወድሟል፤ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተገድቧል፤ ማኅበራዊ ግንኙነት በእጅጉ ተጎድቷል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ታዲያ ቀዳሚውም፣ ተከታዩም፣ የመጨረሻውም አማራጭ ሰላማዊ ውይይት እንደኾነ ይነገራል፡፡

ግጭቱን በሰላም ለመፍታት ይቻል ዘንድ ደግሞ አፈሙዝ የተማዘዙ ወገኖች ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጡ የሰላም ካውንስል በክልሉ ተቋቁሟል፡፡ ወገንተኝነቱ ሰላም እንደኾነ የሚነገረው ይህ የሰላም ካውንስል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ የተቋቋመው የሰላም ካውንስል ተግባር እና ኀላፊነቱን ሲገልጽ “ካውንስሉ በሁለቱም ወገኖች እስካልተመረጠ ድረስ አመቻች እንጂ አደራዳሪ አይደለም፡፡ አመቻች ማለት ሁለቱ ወገኖች እኩል ንግግር እና ድርድር እንዲቀበሉ አደራዳሪ እና ተደራዳሪ እንዲመርጡ፣ ቦታ እና ጊዜ እንዲወስኑ፣ እያለቀ ያለውን ንፁሑን፣ እየተጎዳ ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል ግምት ውስጥ አስገብተው ተኩስ አቁመው እንዲነጋገሩ የማግባባት እና የማመቻቸት ሥራ ይሠራል ማለት ነው፡፡

ካውንስሉ ለየትኛውም ወገን ማዳላት ሳያሳይ በየትኛውም ወገን ጫና ሳይደረግበት ሁለቱም ወገኖች በቅንነት እንዲቀራረቡ እና እንዲደራደሩ የአመቻችነት ሚናውን ይወጣል፡፡ ከየትኛውም ወገን ጣልቃ ገብነት አያስተናግድም” ብሏል፡፡ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ግጭት ሲፈጠር ቢቻል በግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ተወያይተው ካልኾነ ደግሞ በሦስተኛ ወገን ተነጋግሮ ችግሮችን መፍታት ሀገር በቀል ባሕል ነው ይላሉ፡፡

በአማራ ክልል የሰላም ካውንስል መቋቋም ከችግሮች ወደ መፍትሔ ለመምጣት የራሱ የኾነ ፖለቲካዊ ጥቅም ይኖረዋል ነው የሚሉት፡፡ የሰላም ካውንስሉ በተሳካ ሁኔታ ግቡን ለመምታት ከሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት እና አመኔታ ሊኖረው ግድ ይላል፤ ይህ ከሌለ ግን የትም አይደርስም፤ የሁለቱም ወገን ይሁንታ ቅድመ ሁኔታ ነው ይላሉ፡፡

ከሁለቱም ወገኖች በኩል ተቀባይነት እና አመኔታ ካለው ሥራው ስኬታማ ይኾናል ነው ያሉት፡፡ የክልሉን ችግር ለመፍታት የተቋቋመው የሰላም ካውንስል ፋይዳው ትልቅ ነው፤ አንድ እርምጃ ወደፊት መራመድ ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን ይላሉ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ መቋቋሙ ብቻ ግን ችግሩን ሊፈታው አይችልም፤ ችግሮች የሚፈቱት ካውንስሉ የሁለቱን ወገኖች ይሁንታ ማግኘት ሲችል ነው፤ ይሄም አስፈላጊ ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ የአንድ ወገን ይሁንታ ብቻ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ነው፤ ችግሩንም ሊፈታው አይችልም፤ የሁሉም ተቀባይነት መሠረታዊ ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡

በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ይኖራቸው ዘንድ ደግሞ ገለልተኝነታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው ነው የሚሉት፡፡ ለሀገር ያደላ መኾን አለበት የሚሉት መምህሩ ለሀገር ያደላ ማለት ሕዝቡን መሠረት ያደረገ እንጂ የጥቂት ፖለቲከኞችን አስተሳሰብ መሠረት ያደረገ መኾን የለበትም ማለት ነው ብለዋል፡፡ የጥቂት ፖለቲከኞችን ሃሳብ መሠረት ያደረገ ስኬት ላይ ሊደርስ አይችልም ብለዋል፡፡

ነገሮች አልጋ በአልጋ አይኾኑም፣ ይሄ ግልጽ ነው፣ ካውንስሉ ከባድ ኀላፊነትን መሸከም የሚችል መኾን አለበት፣ ከዚያም ከዚህም መገፋፋት እና ማዋከብ ሊኖር ይችላል፤ በሚፈልጉት መንገድ ካልተካሄደላቸው እስከ ማሳደድ ሊደርስ የሚችል ችግር ሊኖር ስለሚችል ከባድ ኀላፊነት መውሰድ የሚችል መኾን አለበት ነው የሚሉት መምህሩ፡፡

የፖለቲካ ችግሮች ያሉት ታችኛው ማኅበረሰብ ላይ አይደለም፤ ችግሮቹ ያሉት ሊሂቃን ላይ ነው የሚሉት መምህሩ የሰላም ካውንስሉ ትኩረቱን ከላይኛው ላይ ማድረግ አለበት፤ ታች ያለው የሚታዘዝ ወይም የሚከተል ነው፤ ዋናው መሪውን ማሳመን ከተቻለ ታችኛውንም ማሳመን ይቻላል ይላሉ፡፡ ትልቁ ችግር ሊህቃኑ ላይ በመኾኑ ካውንስሉ የተሠበሠበ፣ አቅም፣ ብቃት ያላቸው ሰዎችን በማካተት ከላይኛው መዋቅር ላይ በትኩረት መሥራት ይገባዋል ብለዋል፡፡

በትክክለኛው መሠረት ላይ የቆሙ እና ከራስ ፍላጎት እና ዓላማ ጋር የሚተሳሰሩ ትችቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚያነሱት መምህሩ የሰላም ካውንስሉ መድረክ ሲያካሂድ የፖለቲካ ሹመኞችን ወይም በታጠቁ ወገኖች ያሉትን መሪዎች መጋበዝ ላይጠበቅበት ይችላል፤ ዓላማውን፣ ግቡን እና ኀላፊነቱን ራሱ እንዲናገረው ማድረግ የተመረጠው አካሄድ ነው፤ በሚያደርጋቸው መድረኮች የመግቢያ ንግግር ወይም የመዝጊያ ንግግር አንደኛውን ወገን ጠርቶ ቢያስደርግ ጥርጣሬ ውስጥ ይገባል ይተቻልም ብለዋል፡፡

ከሁለቱም ወገኖች ሀገርን መሠረት ያደረገ ውይይት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፤ ከይምሰል ፖለቲካ ከእልኸኝነት ፖለቲካ፣ ከብሽሽቅ ፖለቲካ ወጥቶ ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ውይይት ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት፡፡ እየተጎዳ ያለው ሕዝብ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ወደ ግጭት ያስገባቸው የአሰላለፍ ልዩነት ነው የሚሉት መምህሩ ለሕዝባዊ ትግል ማዕከል መደረግ ያለበት ሕዝብ ነው ብለዋል፡፡ በቅን ልቦና ላይ የተመሠረተ የሕዝብ አገልጋይነት ስሜት መፈጠር እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

አንደኛው ሌላኛውን በቃላት ጦርነት በልጦ ለመገኘት ሳይኾን ዘላቂ የኾነ ኅብረተሰባዊ እረፍት የሚሰጥ ነገርን ማሰብ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡ ሕዝብን የሚያስጨንቁ አካሄዶችን ማቆም፣ ሰፊውን ሕዝብ ማዳመጥ፣ በነባራዊ ሁኔታ በመመሥረት የሕዝብን ፍላጎት ማዳመጥ ከሁለቱም ወገኖች ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

መንግሥት ለተቃውሞ የሚያበቁ ችግሮችን መፍታት እና ማስተካከል እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡ ለተቃውሞ ምቹ የኾኑ ችግሮችን መፍታት ሲገባ በተቃራኒው ከተሄደ ግን ሁሉንም ወደ ሚጎዳ ችግር ያስገባል ነው የሚሉት፡፡ በሁለት ወገን ለመጥቀም የሚፈልጉ የፖለቲከኛ ሹሞችን ማጥራት፣ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አሠራሮችን መዘርጋት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ እርምጃዎች ናቸው ይላሉ፡፡

በታጠቁ ወገኖችም ግጭት ለችግር መፍቻ የመጀመሪያው ምርጫ መኾን እንደማይገባውም አመላክተዋል፡፡ ለድርድር የሚቀመጡባቸውን እና የማይቀመጡባቸውን ጉዳዮች ለይቶ ማሳወቅ ይገባል እንጂ ሙሉ ለሙሉ አንደራደርም ማለት የሕዝብን ሰቆቃ ያራዝማል እንጂ መፍትሔ አይኾንም ነው የሚሉት፡፡

አሁን ባለው የፖለቲካ ልምምድ እና አካሄድ ወደ ፖለቲካው የማይቀርቡ ወይም ፖለቲካው የማያስቀርባቸው የተረሱ አካላት አሉ የሚሉት መምህሩ የእነዚህን ወገኖች ሃሳብ ማድመጥ ትልቅ ጥቅም አለው ይላሉ፡፡ አሁን ላይ ለሀገር ይበጃል የምትለውን ሃሳብ በነጻነት መናገር አይቻልም፣ ሃሳብህ አንደኛውን ወገን የሚደገፍ መስሎ ከታዬ ጥቃት ይደርስብሃል፤ የሃሳብ ልዩነት መከበር እና መስተናገድ አለበት ነው የሚሉት፡፡ በሃሳብ የተለዩትን ሰዎች የተለየ ድርጊት እንደፈጸሙ አድርጎ መቁጠር ልክ አይደለም፤ ሁለቱም ወገኖች የሃሳብ ልዩነትን ማክበር ግድ ይላቸዋል ነው ያሉት፡፡

ከሁለቱም ወገኖች የተለየ ሃሳብ ያለው ሰው ሊኖር እንደሚችልም ማሰብ መቻል አለባቸውም ይላሉ፡፡ የሰላም ካውንስሉ የማመቻቸት ሥራ ስኬታማ ከኾነ ሀገር እና ሕዝብ የሚያተርፉት ትርፍ ከፍ ያለ ነው፤ ለሕዝብ ትልቅ እረፍት ነው፣ ሰላማዊ የኾነ አንድ ቀንም ዕድሜ ነው ብለዋል፡፡ ሰላም ካለ በየቤቱ ደስታ አለ፣ የተፈጠረው ምጣኔ ሃብታዊ ምስቅልቅልም ይፈታል ነው ያሉት፡፡

ለስኬታማነቱ ደግሞ የተቋቋመው የሰላም ካውንስል በግልጽ ገለልተኛነቱን ማሳየት አለበት፣ ሁሉንም ወገኖች አዳምጦ የመሥራት ኀላፊነት አለበት ብለዋል፡፡ ሁለቱም ወገኖች ሕዝቡ እንዲህ ነው ሃሳቡ፣ እንዲህ ነው ፍላጎቱ ከማለት ይልቅ የሕዝቡን መሠረታዊ ፍላጎት ማዳመጥ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት፡፡

የሕዝብን ትክክኛ ፍላጎት በተለያዬ መንገድ ማዳመጥ፣ መለየት ያስፈልጋል፤ በጅምላ የሕዝብ ፍላጎት ይሄ ነው ብሎ መናገር ግን ትክክለኛ አካሄድ አይደለም ብለዋል፡፡ ሁለቱም ወገኖች ከእልህ፣ ከብሽሽቅ እና ከማስመሰል ወጥተው ለሕዝብ ማሰባቸውን በተግባር ማሳየት እንደሚገባቸውም አመላክተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአረንጓዴ አሻራ ልማት ንቅናቄ የፍራፍሬ ተክሎች የማልማት ሥራ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናገሩ።
Next articleበርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የተመራ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ልዑክ ለሥራ ጉብኝት ጎንደር ከተማ ገባ።