
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 29/2012 ዓ.ም (አብመድ) የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር አስተባባሪ አቶ አበበ ሲሳይ የኮሮና ቫይረስን የመከላከል ሥራው በበጎ ፍቃደኞች በሚሰጥ ትምህርት እና የእጅ መታጠቢያ ቦታዎችንና ግብዓት በማቅረብ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
በዞኑ ‘‘እስከ ዛሬ ረፋድ ድረስም ምንም ዓይነት ተጠርጥሮ ክትትል የሚያደርግ ሰው የለም’’ ያሉት አቶ አበበ ባለፉት ቀናት ተጠርጥረው መጥተው የነበሩ ዜጎች በምርመራ ከቫይሱ ነጻ ሆነው መመለሳቸውንም ተናግረዋል፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን አሁንም የመከላከል ሥራው ውጤታማነት ላይ ስጋቶች እንዳሉ ያመለከቱት አቶ አበበ ከአዲስ አበባ ወደ ወልዲያ የሚደረጉ የሌሊት ጉዞዎች መኖር ፈታኝ እንደሆነባቸው አንስተዋል፡፡ በኅብረተሰቡ የሚታየው አካላዊ ርቀትን አለመተግበር ስጋት ሁኖ መቀጠሉንም ነው የተናገሩት፡፡ ‘‘የኅብረተሰቡ ጤንነት ለማረጋገጥ መንግሥት እና በጎ ፍቃደኞች አሁንም በከተማዋ በከፍተኛ አደረጃጀት እየሠሩ ቢሆኑም ሕዝቡ ከቸልተኝነት አስተሳሰብ በመውጣት ራሱን በመጠበቅ ካላገዛቸው ስጋት መሆኑ አይቀርም’’ ብለዋል፡፡
ወደዞኑ የገቡ የሙቀት መለኪያ ቴርሞ ሜትሮችን የትክክለኝነት ንባብ የሚያረጋግጡ ባለሙያዎች ከክልል መጥተው ባለማየታቸው ወደሥራ ማስገባት አለመቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሞገስ መርካ ደግሞ በአስተዳደሩ ቫይረሱ እንዳለባቸው ከተጠረጠሩ ሦስት ሰዎች መካከል ሁለቱ ዛሬ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው የአንዲት ተጠርጣሪ የምርመራ ናሙና ትናንት ወደደሴ መላኩንም ገልጸዋል፡፡
በአስተዳደሩ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የነጋዴዎች እና የነዋሪዎች በጎ ፍቃደኝነት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ትናንት 20 የሚደርሱ የሙቀት መለኪያ ቴርሞ ሜትሮችን ለሁሉም ወረዳዎች ማሠረጨታቸውን የተናገሩት አቶ ሞገስ የቴርሞ ሜትሮቹ ሥራ መጀመር ጥርጣሬዎችን ለማጥራት ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡
እንደሰሜን ወሎ ዞን ሁሉ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርም ሕገ ወጥ የሰዎች የሌሊት ትራንስፖርቶች ለንክኪ ስለሚያጋልጥ እና ቫይረሱን ከቦታ ቦታ በቀላሉ ስለሚያዘዋውረው ስጋት መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
አካላዊ መራራቅ በመፍጠር ረገድ ከጊዜ ወደጊዜ ለውጦች ቢኖሩም አሁንም መዘናጋቶች እና ሙሉ በሙሉ መጠንቀቅ ላይ ክፍተቶች በመኖራቸው ለቫይረሱ መጋለጥ አንዱ የስጋት ምንጭ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ዜጎችን ለመታደግ የተከለከለው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በሌሊት ጉዞዎች ተተክቶ ለአላስፈላጊ እንግልትና ወጭ ከሚዳርግ በሽታውንም በቀላሉ እንዲስፋፋ ከሚያደርግ ሕጋዊ አሠራሮችን እንደአማራጭ ማምጣት ወይም በኬላዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ አብመድ ከዞኖቹ ታዝቧል፡፡
አካላዊ መራራቅን መተግበር ነገን ለማየት ካለን ፍላጎት ጋር ማስተሳሰር ያስፈልጋል፡፡ ኅብረተሰቡ መውደዱንና ናፍቆቱን የሚገልጠው በዛሬ መጠጋጋት እና ቸልተኝነት ሳይሆን በእምነት የነገ ተስፋዎቹን እውን ለሚያደርግለት ዓላማ መሠዋዕትነት መክፈል ያስፈልጋል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ