
ባሕር ዳር: ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በጎንደር ከተማ በፌደራል እና በክልሉ መንግሥት እየተገነቡ የሚገኙ መሰረተ ልማቶችን በከተማዋ ተገኝተው ተመልክተዋል። በጉብኝታቸው የመገጭ ግድብ፣ የአዘዞ አርበኞች አደባባይ የመንገድ ግንባታ፣ ጥገና እየተደረገለት የሚገኘውን የአጼ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥት እና የኮሪደር ልማቱን ሂደት ተመልክተዋል።
በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክትትል የሚደረግባቸው የከተማዋ ፕሮጀክቶች ለውጥ እያመጡ መኾናቸውን በምልከታቸው እንዳረጋገጡ ገልጸዋል። በ18 ወራት መጠናቀቅ እንዳለበት አቅጣጫ የተቀመጠለት የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ እየተፋጠነ እንደሚገኝ ያነሱት አቶ መላኩ ለፕሮጀክቶቹ መጓተት እንቅፋት የነበረው የግንባታ እቃዎች አቅርቦት ችግር መፈታት መቻሉ ሥራው እንዲፋጠን ማድረጉን ገልጸዋል።
ከአዘዞ- አርበኞች አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት እና ከመገጭ ግድብ ፕሮጀክት በተጨማሪ የፋሲል አብያተ ቤተ መንግሥታት ጥገና እና የኮሪደር ልማቱም በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ በሚያስችል መልኩ እየተሠራ እንደሚገኝም አመላክተዋል። በከተማዋ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ለመጓተታቸው ዋነኛ ምክንያት የልማት ቦታዎችን ከሦስተኛ ወገን ነጻ የማድረግ ችግር እንደነበር ያነሱት ሚኒስትሩ አሁን ላይ በማኅበረሰቡ ከፍተኛ እገዛ ችግሩን መቅረፍ ተችሏል ብለዋል።
በከተማዋ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የፌደራል መንግሥቱ ክትትል እና ድጋፍ እንደሚያደርግም አቶ መላኩ ገልጸዋል። በጎንደር ከተማ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የከተማዋ መሪዎች ቁርጠኛ ኾነው እየሠሩ እንደሚገኙ የጎንደር ከተማ አሥተዳድር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ገልጸዋል።
የፌደራል መንግሥት ለከተማዋ ፕሮጀክቶች የሰጠው ትኩረት የሚመሰገን መኾኑንም ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል። በኮሪደር ልማቱ ተነሺ የኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለማቋቋም ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ እንደሚገኝም ምክትል ከንቲባዋ አስታውቀዋል።
በደስታ ካሣ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!