ያላግባብ ዋጋ የጨመሩ ተቋማት ላይ እርምጃ እየተወሰዱ መኾኑ ተገለጸ።

13

ባሕር ዳር: ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሕገ ወጥ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ እና ምርትን የማከማቸት ተግባራት ዙሪያ እየተደረገ ያለው ክትትል እና ቁጥጥር ተጠናክሮ መቀጠሉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ደ.ር) አስታወቁ። በዛሬው እለት ብቻ ያላግባብ ዋጋ የጨመሩ 217 ተቋማት ታሽገዋል። የአንድ ተቋም የንግድ ፍቃድ የተሰረዘ መኾኑንም ተናግረዋል። እንዲሁም ምርት የደበቁ ስምንት የንግድ ተቋማት ሲታሸጉ፤ ሦስት ተቋማት ደግሞ ፍቃዳቸው ተሰርዟል ብለዋል።

በሌላ በኩል የሕግ ጥሰት ፈጽመው በመገኘታቸው ታሸገው ከነበሩ የንግድ ተቋማት መካከል 27 ሺህ 78ቱ ተከፍተው ወደ ሥራ መመለሳቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ሚንስትሩ አያይዘውም እስካሁን የእስራት እርምጃ ከተወሰደባቸው 430 ነጋዴዎች ውስጥ 122 በሠሩት ስህተት ተጸጽተው ለመታረም ዝግጁ በመኾናቸው ከእስራት ተፈተዋል፡፡

በግንባታ እቃዎች ላይ ሕገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ 217 ተቋማት ሲታሸጉ የአንድ ተቋም ፍቃድ ሙሉ በሙሉ መሰረዙን ካሳሁን (ዶ.ር) ገልጸዋል። ምርት በሕገ ወጥ መንገድ ያከማቹ ስምንት ተቋማት ሲታሸጉ የሦስት ተቋማት ፍቃድ መሠረዙንም ሚኒስትሩ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ የተገኘ መረጃ ያሳያል።

በተደረጉ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎች ምክንያት በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በምግብ ዘይት፣ በዱቄት፣ ስኳር፣ ቲማቲም፣ ድንች እና በመሳሰሉት ምርቶች ላይ የዋጋ መረጋጋት የታየባቸው ሲኾን ዋጋ የማረጋጋት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በኢትዮጵያ በተለይ በኢነርጂ ዘርፍ የታየው ተስፋ ሰጪ ውጤት ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው” የኢራን አምባሳደር አሊ አክባር
Next articleበጎንደር ከተማ የተጀመሩ መሰረተ ልማቶች በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተናገሩ።