
ባሕር ዳር: ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍስሀ ይታገሱ (ዶ.ር ) በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር አሊ አክባርን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ውይይት አድርገዋል። በውይይታቸውም ሁለቱ ጥንታዊ ሀገራት ያላቸውን የረጅም ጊዜ የጠበቀ ግንኙነት በኢንቨስትመንት ማጠናከር በሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ዙሪያ ሀሳብ ተለዋውጠዋል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ (ዶ.ር) ፍስሀ ሁለቱም ሀገራት የብሪክስ አባል መኾናቸው ለኢንቨስትመንት ግንኙነቱ የጀርባ አጥንት እንደሚኾን ተናግረዋል። ኮርፖሬሽኑ በሚያሥተዳድራቸው የኢንቨስትመንት ማዕከሎች ውስጥ ባለሀብቶች ብዝኃነት እንዲኖራቸው ለማድረግ በመላው ዓለም የሚገኙ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶችን አሟጦ ለመጠቀም እያደረገ በሚገኘው እንቅስቃሴ ኢራንም ተሳታፊ እንድትኾን ፍላጎት እንዳለ አረጋግጠዋል።
ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ማኀበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ዶክተር ፍስሀ በቀጣይ የኢትዮ-ኢራን ኢንቨስትመንት ፎረምን ማዘጋጀትን ጨምሮ ሌሎች አጋዥ ሥራዎችን በጋራ መሥራት እንደሚገባ አንስተዋል። በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር አሊ አክባር “በኢትዮጵያ በተለይ በኢነርጂ ዘርፍ የታየው ተስፋ ሰጪ ውጤት ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው” ብለዋል።
የኢራን ባለሀብቶች በተለይም በአግሮ ፕሮሰሲንግ እና በተሽከርካሪ ማምረት እና መገጣጠም ዘርፍ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንደሚሠራም አክለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!