ብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል የሙያ ብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ገለጸ።

16

ባሕር ዳር: ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሙያ ብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ ኤጀንሲ በ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ውይይት አካሂዷል። የ2017 በጀት ዓመት እቅድም ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ የሽዋስ እንዳሉት ኤጀንሲው የኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል። በ2016 በጀት ዓመትም ለመደበኛ ሠልጣኞች እና በኢንዱስትሪዎች ለሚሠሩ ሙያተኞች የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጥ ሥራ ተሠርቷል። ለዜጎች አጫጭር ሥልጠናዎችን በመስጠት ወደ ውጭ ሀገር ለሥራ እንዲሄዱ ተደርጓል።

ይሁን እንጅ በበጀት ዓመቱ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተቀመጡ እቅዶችን ለማሳካት አለመቻሉን ገልጸዋል። የኤጀንሲው እቅድ እና በጀት ዳይሬክተር ተጋረድ ዘሪሁን ባለፉት ዓመታት በዝቅተኛ እና መካከለኛ ደረጃ የሚገኘውን የሰው ኃይል እና የመደበኛ ሠልጣኞችን ብቃት በማረጋገጥ ወደ ኢንዱስትሪው እንዲቀላቀሉ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

በ2016 በጀት ዓመት 14 ሺህ 500 የሚኾኑ መደበኛ ሠልጣኞችን ብታት ለማረጋገጥ ታቅዶ 61 በመቶ የሚኾነውን በክልሉ በሚገኙ ስድስት የክላስተር ተቋማት የማረጋገጥ ሥራ ተሠርቷል። በመካከለኛ እና ዝቅተኛ ደረጃ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ለተሰማሩ 2 ሺህ 982 ባለሙያዎችም ምዝና መሰጠቱን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት። ለ131 አዲስ መዛኞችንም ማፍራት ተችሏል።

ደብረ ማርቆስ ክላስተር አጫጭር ሥልጠና በመስጠት፣ ጎንደር፣ ደሴ እና ወልድያ ክላስተሮች ደግሞ መዛኝ በማፍራት እና የምዘና ማዕከል በማደስ የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸው ናቸው። በ2017 በጀት ዓመት የምዘና ተደራሽነትን በማስፋት እና ምዘናውን ፍትሐዊ ለማድረግ እንዲሁም መደበኛ እና አጫጭር ሥልጠናዎችን በተጠናከረ መንገድ ለመሥጠት ታቅዶ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ኤጀንሲው ባለፉት ዓመታት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የበቁ ባለሙያዎችን ብቃት በማረጋገጥ ወደ ኢንዱስትሪዎች እንዲቀላቀሉ አድርጓል። በቀጣይ የተሻለ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ለማሠልጠን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ቀን ከሌሊት ለሀገራችን ብንሠራ ሽልማታችን በምድርም በሰማይም ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“በኢትዮጵያ በተለይ በኢነርጂ ዘርፍ የታየው ተስፋ ሰጪ ውጤት ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው” የኢራን አምባሳደር አሊ አክባር