“ቀን ከሌሊት ለሀገራችን ብንሠራ ሽልማታችን በምድርም በሰማይም ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

47

ባሕር ዳር: ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከመገናኛ እስከ ሲ.ኤም.ሲ ያለውን የኮሪደር ልማት ለአገልግሎት ክፍት ባደረጉበት ወቅት የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ይህ መስመር በባቡሩ ምክንያት የቆሻሻ ማስወገጃዎችን እና ፍሳሾችን ለመሥራት፣ ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ የማገናኘት ሥራው ከከዚህ ቀደሞቹ በጣም አስቸጋሪ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

መስመሩ አረንጓዴ ቦታዎችን፣ የልጆች መጫወቻ ቦታዎችን፣ ሰዎች አረፍ ብለው የሚያነቡባቸውን እና የሚያሰላስሉባቸውን ቦታዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን እና የሕንጻ ውበትን አካትቶ መያዙንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ አበባዎችን፣ አረንጓዴ ቦታዎችን እና ዛፎችን የያዙ ንፁህ እና ሰፊ ቦታዎች የሰፋ አስተሳሰብ እንዲኖረን ያደርጉናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንደዚህ ዓይነት አካባቢዎች የነገ ሀገር ተረካቢ የኾኑት ተማሪዎች አሰላሳይ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡

ለአካባቢው ሰዎች ደግሞ መገናኛ እና ሰብሰብ ብለው የጋራ ጉዳዮቻቸውን የሚጨዋወቱበትን ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም እንደዚህ ዓይነት ቦታዎች ኪስ ቦታዎች ሲባሉ እንደነበር የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ቦታዎቹ ገንዘብ ለመሰብሰብ ይቸበቸቡ የነበረ ቢሆንም ከሽያጩ የሚገኘው ገንዘብ ግን ለከተማው ልማት ውሎ እንደማያውቅ ገልጸዋል፡፡

እስካሁን አምስት ኮሪደሮች ተሠርተዋል፤ እነዚህን ሙሉ በሙሉ ስናጠናቅቅ ልማቱን በሌሎች አካባቢዎች ለመቀጠል ጥናቶች ተጠናቅቀዋል ብለዋል፡፡ ሀሳባችን አዲስ አበባ አረንጓዴ ቦታዎች፣ አበባዎች እና ዛፎች በየቦታው የሚታዩባት፣ ልጆች የሚቦርቁባት፣ ለመኖር ምቹ የሆነች ማድረግ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ከተማዋን ከተደረተው የከተማ ሥርዓት ከፈትፈት ወዳለ የከተማ ሥርዓት ለመለወጥ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። “ጅማሮው ተስፋ የሚሰጥ ቢሆንም ገና ብዙ ነገር ስለሚጠበቅብን በዚህ ጅማሮ ረክተን መዘናጋት የለብንም” በማለትም ቀጣይ ዓላማቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ ሥራ ለሁሉም ጠቃሚ ስለኾነ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ትዕግስት እና ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ሥራ ማለት የሰውን ሕይወት ማሻሻል፣ ድህነትን መቀነስ፣ የሥራ ዕድልን መፍጠር፣ መሰረተ ልማት መዘርጋት መኾኑን ስለምናውቅ ለአልባሌ ነገር የምንሰጠው ጊዜ የለንም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

“በማውራት የሚበሉ አሉ፣ በመሥራት የምንኖርም አለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “በማውራት የሚኖሩ ሰዎች የእንጀራ ገመዳቸው እያጠረ እንጂ እየቀጠለ ስለማይሄድ ምርጫው የኛ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። በሥራ መኖር የሚፈልጉ ሰዎች እንጀራቸው እየሰፋ ዕውቀታቸው እየዳበረ ስለሚሄድ መሥራት አያጎድልም፣ መሥራት አያከስርም ብለዋል። “ሁላችን ቀን ከሌሊት ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ብንሠራ ሽልማታችን በምድርም በሰማይም ነው” በማለት በሥራ የሚገኘውን ውጤት ገልጸዋል፡፡

ይህ ሥራ በጣም አድካሚ እና ጭቅጭቅ የነበረበት ቢሆንም ውጤቱ ግን ያማረ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የዛሬ አምስት ዓመት በተደረገ ጥናት የአዲስ አበባ የአረንጓዴ ቦታ ስፋት ከ2 በመቶ እንደማይበልጥ ጠቅሰዋል። አሁን ግን ወደ 20 በመቶ እየቀረበ ነው ብለዋል፡፡ የአዲስ አበባ አረንጓዴ ሥፍራን ዕድገት ማረጋገጥ የፈለገ ሰው ከቦሌ እስከ ጎሮ ያለውን መስመር ብቻ ተመልክቶ ማረጋገጥ እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በኋላ አዲስ አበባ ለመኖር የምታጓጓ ምቹ ከተማ ትሆናለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፤ እጅግ ታታሪ እና አቃፊ ሕዝብ ስላለን ሕዝቡን የሚመጥን ነገር ከሠራን ከተማዋን የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ እንችላለን ብለዋል፡፡ ስለዚህ ከወሬ ይልቅ ሥራን እንድናስቀድም፣ ከፕሮፖጋንዳ ይልቅ የሚታይ የሚጨበጥ እንድናይ አደራ እላለሁ ብለዋል፡፡

“እየሠሩ እና እየደከሙ ድካማቸው በአሉባልታ የተሸፈነባቸው ሰዎች ካሉ ሥራቸው በደንብ እየታየ፣ የሚያወሩት እየከሰሩ የምንሠራው እያተረፍን ስለምንሄድ ትኩረታችን እርካታ የሚያስገኝ ሥራ ላይ መሆን አለበት” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጠንክረን ኢትዮጵያን በማበልፀግ የድህነት ስሟን ፍቀን የበለፀገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን እናስረክባለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሥራ ኀላፊዎች በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተገኝተው የሥራ እና የልምድ ልውውጥ አካሄዱ።
Next articleብቃት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል የሙያ ብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ገለጸ።