
ባሕር ዳር: ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሥራ ኀላፊዎች የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዘረጋቸውን ዘመናዊ እና ዲጅታል የችሎት አገልግሎት መስጫዎችን ተመልክተዋል። በልምድ ልውውጡ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እና ሌሎች የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በቆይታቸው በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን እና የሥራ እንቅስቃሴዎችን፣ ዘመናዊ የኢ-ኮርት ወይም በቴክኖሎጂ የታገዘ የችሎት አገልግሎት አሰጣጥን እና ሌሎች የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴዎች ጉብኝተዋል። የጉብኝቱ የልዑካን ቡድን አባላት የ2016/17 በጀት ዓመት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዋና ዋና ተግባራትን እና ሌሎች የተቋሙ ዲጂታል አገልግሎቶችን አስመልክቶ በተለያዩ የሥራ ኀላፊዋች ማብራሪያ ቀርቦ ተሞክሮውን ወስደዋል።
ለአዲስ ተሿሚዎች መልካም የሥራ ዘመን ምኞታቸውን የገለጹት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ቴዎድሮስ ምህረት በቀጣይ የሥራ ዘመን የተገልጋዩን የፍትሕ ፍላጎት ያማከሉ ሥራዎች እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡ የተጣለባቸውን ኀላፊነት እንደሚወጡ ምኞታቸውን የገለጹት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንቱ ለሥራቸው ስኬትም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጎናቸው በመኾን እገዛ እና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት አለማንተ አግደው በዲጂታል የታገዘ የክልሉን ሕዝብ ተደራሽ የሚያደርግ የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ ጅማሮ እንዳለ ተናግረዋል። “በልምድ ልውውጡ ያገኘናቸውን ተሞክሮዎች በመውሰድ በክልሉ ተግባራዊ ለማድረግ እንሠራለን” ብለዋል። በሥራዎቻቸውም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጎናቸው በመኾን ድጋፎችን እንዲያደርግም ነው የጠየቁት።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለቀጣይ ሥራዎች ግብዓት የሚኾን የሥራ እና የልምድ ተሞክሮ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!