
ባሕር ዳር: ነሐሴ 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የመገጭ የመስኖ እና የመጠጥ ውኃ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መኾኑን መመልከታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገልጸዋል። ሚኒስትሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አመራር ሰጪነት ዳግም የተጀመረውን ፕሮጀክት የግንባታ ሂደት ያለበትን ደረጃ ተመልክተዋል።
ሚኒስትሩ የፕሮጀክቱ ዳግም መጀመር የጎንደር ከተማን የመጠጥ ውኃ ችግር በዘላቂነት በመፍታት የሕዝቡን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ነው ብለዋል። ጎንደር ከተማ የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝም እና የንግድ ማዕከል እንደመኾኗ መጠን ልማቷን የሚያፋጥኑ ፕሮጀክቶች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱን በአጠረ ጊዜ አጠናቅቆ ለአገልግሎት ለማብቃት መንግሥት ተገቢውን ክትትል እና ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም አስረድተዋል። በአዲስ ተቋራጭ የተጀመረው የግድቡ ግንባታ በጥሩ የአፈፃፀም ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል፡፡ ተቋራጩ ግንባታውን በፍጥነት እና በጥራት እንዲያጠናቀቅ ተገቢ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል።
የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አመራር ሰጭነት ተጓተው የቆዩ የልማት ፕሮጀክቶች ዳግም መጀመር በኅብረተሰቡ ዘንድ ደስታን ፈጥሯል። የፌዴራል እና የአማራ ክልል መሪዎች የሚያደርጉት ያልተቋረጠ ክትትል ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር እንደኾነም ተናግረዋል።
አቶ መላኩ አለበል በጉብኝታቸው የከተማውን የኮሪደር ልማት፣ የአጼ ፋሲል አብያተ መንግሥት ዓለም አቀፍ ቅርስ የጥገና ሥራ እንዲሁም የአዘዞ ጎንደር የኮንክሪት አስፋልት መንገድ የሥራ እንቅስቃሴን ይመለከታሉ ተብሎ ይጠበቃል። የመገጭ የመስኖ እና የመጠጥ ውኃ ግድብ ርዝመት 77 ሜትር ከፍታው ደግሞ 19 ሜትር ሲኾን ውኃ የመያዝ አቅሙም 185 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ነው።
እንደ ኢዜአ ዘገባ በጉብኝቱ የከተማው ከፍተኛ መሪዎች እና የልማት ፕሮጀክቶቹ ኀላፊዎች ተሳታፊ ኾነዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!