”የቴክኖሎጂ መራቀቅ ለሀሰተኛ መረጃዎች ሥርጭት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተገንዝቦ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል” የጋዜጠኝነት እና ሥነ-ተግባቦት መምህርት ሕይወት ዮሐንስ

10

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቴክኖሎጂ መራቀቅ ለሰው ልጅ ኑሮን ቀለል ለማድረግ የሚያግዘውን ያክል በጥንቃቄ እና በዕውቀት ካልተያዘ ለጥፋት ዓላማ እንደሚውል ይገለጻል። ኒዩክሌር ለኃይል አቅርቦት እንደሚያገለግል ሁሉ ለሰው ልጅ ጅምላ ፍጅትም እንደሚውለው ማለት ነው።
በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂው ዘርፍም በየጊዜው የሚፈጠረው ግኝት በዲጂታል ሚዲያው ዘርፍ የሚኖረውን ተግባቦት የበለጠ ያሳለጠው ቢኾንም በዚያው ልክ ችግሮችን አስከትሎ መጥቷል።

ለዛሬው በማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፍ በሀሰተኛ ማንነት ሀሰተኛ መረጃ ስለመልቀቅ እና መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች የዘርፉን ምሁር ሙያዊ ምክር ተቀብለናል። መምህርት ሕይወት ዮሐንስ ይባላሉ። በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ሥነ- ተግባቦት መምህርት ናቸው። በማኅበራዊ ሚዲያ በተለይም በፌስ ቡክ ሀሰተኛ አካውንት በመጠቀም ስለሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎች እና የጥንቃቄ አማራጮቹ ማብራሪያ ሰጥተውናል።

መምህርት ሕይወት ሀሰተኛ ገጾችን (fake accounts) የሚጠቀሙ ሰዎች ድብቅ የፖለቲካ፣ ምጣኔ ሃብት እና ማኅበራዊ ግለ ጥቅም ያላቸው ሰዎች ናቸው ይላሉ። እነዚህ ሰዎች የማኅበረሰቡን ትክክለኛ መረጃ የማግኘት መብት በመጋፋት ያልተገባ፣ የተዛባ እና ሀሰተኛ መረጃ ሊያሰራጩ እንደሚችሉ ይናገራሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሚዲያ ተቋማትን፣ የባለሥልጣናትን እና የታዋቂ ሰዎችን የፌስቡክ አካውንት በመጥለፍ ወይም በማስመሰል መረጃዎችን ማሠራጨት መጀመሩን መምህርት ሕይወት ጠቅሰዋል። በቴክኖሎጂ መዘመን ሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial Intellegence) የሚባለው ቴክኖሎጂ መምጣቱ ደግሞ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለማሠራጨት ሰፊ እድል መፍጠሩን ያብራራሉ። ሰው ሠራሽ አስተውሎት የአንድን ሰው ድምጽ፣ ምስል እና እንቅስቃሴ አስመስሎ ማቀናበር ያስችላል። ሰዎች ያላሉትን እንዳሉ፤ ያልተገኙበት ላይ እንደተገኙ፣ ያላደረጉትን እንዳደረጉ አስመስሎ መሥራት ያስችላል። ስለኾነም በቀጣይ ኅብረተሰቡን ብቻ ሳይኾን የጋዜጠኝነት ሙያን ጭምር ፈተና ውስጥ እንደሚከተው ጠቁመዋል።

የኅብረተሰቡ የሚዲያ እውቀት አለመዳበር ለአጭበርባሪዎች ምቹ ሁኔታ መኾኑን መፍጠሩን ጠቅሰዋል። በማኅበራዊ ሚዲያ የተለቀቀው ሁሉ እውነት ነው ብሎ የሚያምን ማኅበረሰብ አሁንም በርካታ መኾኑን አንስተዋል። የማኅበራዊ ሚዲያ ሀሰተኛ መረጃን ለመከላከልም ግለሰቦችም ኾኑ ተቋማት የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶቻቸውን በጥንቃቄ መያዝ እንዳለባቸው ነው መምህሯ ያሳሰቡት። ተቋማትም የማኅበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎቻቸውን ማሠልጠን አለባቸው ብለዋል።

ግለሰቦችም ኾኑ የሚዲያ ተቋማት የሚያገኙትን ፎቶ እና ቪዲዮ ትክክለኛነት ደጋግመው በመመርመር ማረጋገጥ አለባቸው። የአንድን የማኅበራዊ ሚዲያ የይዘት ትክክለኛነት ለማረጋጥ፦

👉 መረጃውን ያሠራጨው ማን ነው?
👉 መረጃው ትክክለኛ ነው አይደለም?
👉 በዚያ ጊዜ ማሠራጨት ለምን አስፈለገ?
የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ እንደሚያስፈልግ ነው መምህሯ ያመላከቱት።
ቀጥሎም ፕሮፋይሉን (የግል መረጃዎችን) ማየት ያስፈልጋል ያሉት መምህርት ሕይወት በተለይ፦
👉 የአካውንቶችን ዲጂታል መታወቂያ መለየት፣
👉 መረጃውን ያሠራጨው አካል የተጠቀመው ፎቶ፣ ምስል፣ ማንነት እና ምንነት፣
👉 የባለቤቱን ስም (User name)
👉 በተደጋጋሚ የሚለቃቸውን መረጃዎች፣
👉 ዝርዝር የሕይወት መረጃዎቹን፣
👉 ከማን ጋር ተደጋጋሚ የጓደኝነት እና የመረጃ ልውውጥ እንዳለው ማየት፣ ማስተዋል እና ማገናዘብ የመረጃ አሠራጪውን ማንነት ለማወቅ እንደሚያግዙ ዘርዝረዋል።

ማንነቱ ባልታወቀ፣ በባለሥልጣናት እና ታዋቂ ሰዎች ስም እና ምስል ሀሰተኛ አካውንት በመክፈት የሚለቀቀው መረጃ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ተጠቅሞ ከሚለቀቀው ሀሰተኛ መረጃ አኳያ ሲታይ በቀላሉ ሊታወቅ እና መከላከል የሚቻል ነው ብለዋል መምህሯ። የቴክኖሎጂው መራቀቅ ምስሉ፣ ንግግሩ ወይም እንቅስቃሴው የኔ አይደለም ብሎ ለማሳመንም እንደሚያስቸግርም ገልጸዋል። እውነቱን ለማረጋገጥም ሌሎች ውስብስብ መተግበሪያዎችን (applications) እንደሚጠይቅ ጠቅሰዋል።

በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተዘጋጁ ሀሰተኛ ምስሎች፣ ድምጾች እና እንቅስቃሴዎችን በመጠቀም የተለቀቁ መረጃዎችን ደግሞ
👉 thispersondoesn’texist.com
generated.photos/face/white-race/female
👉 Mid journey.com/home
openai.com/dall-e-2
faceapp.com

እና የመሳሰሉትን መለያ ድረ ገጾች በመጠቀም ትክክለኛነታቸውን መለየት እንደሚቻል ገልጸዋል። በተለይ ሚዲያዎች እና ጋዜጠኞች ከመጠቀም በፊት ማረጋገጥ እንዳለባቸው መክረዋል። መምህርት ሕይወት ሁልጊዜ ያልተረጋገጠ፣ ለአንድ ወገን ያደላ፣ ተዓማኒነት የሌለው መረጃ የሚለቅቁ እና የሃሳብ ብዝሃነትን የማያስተናግዱ የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶችን መረጃ አምኖ ከመቀበል በፊት በደንብ መመርመር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አስተውሎ ያልመረመረ ማኅበረሰብ የተደገሰለት አጀንዳ እና ጥፋት ሰለባ ይኾናል። እናም ‘ሳይቃጠል በቅጠል’ ነው መሠራት ያለበት ብለዋል። መምህርት ሕይወት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣንን ጨምሮ ሚዲያዎች እና ጋዜጠኞች መተግበሪያዎቹን በመጠቀም መረጃ መለየት እንደሚቻል የማስተዋወቅ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

ኅብረተሰቡ በማኅበራዊ ሚዲያ ስለሚለቀቁ መረጃዎች ዓይነት፣ ጥቅም እና ጉዳት እንዲሁም መድረግ ስለሚገባው ቅድመ ጥንቃቄ መሠረታዊ የሚዲያ እውቀት እንዲኖረው ማስቻል እንደሚገባም አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ውድ ባለተሰጥዖዎች፣ የኢትዮጵያችን ጥንካሬ በእናንተ እድገት ላይ የተመሠረተ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next article“የመገጭ የመስኖ እና የመጠጥ ውኃ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ በጥሩ ሂደት ላይ ነው” አቶ መላኩ አለበል