
ባሕር ዳር: ነሐሴ 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልእክት በዛሬው ፈጣን ዓለም ባላሰለሰ ትምህርት እና የክህሎት እድገት ውስጥ መሳተፍ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እጅግ አስፈላጊ ኾኗል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው በእረፍት ላይ ላላችሁ ተማሪዎች፣ ለወጣት ባለሞያዎች፣ ራሳቸሁን በእውቀት በመገንባት በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ በጎ ተፅዕኖ ለመፍጠር ለምትጓጉ ሁሉ የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ፕሮጀክት ቀዳሚ ሊያደርጋችሁ ተሰናድቶላችኋል ነው ያሉት።
የትምህርት እና የእውቀት መነሻችሁ እና ያላችሁበት ደረጃ ምንም ይሁን ያላችሁን ክህሎት ለማሳደግም ኾነ አዲስ ነገር ለማወቅ ለምትሹ ሁሉ ሰፊ የእድል በር ተከፍቶላችኋል ብለዋል።
በመላው ኢትዮጵያ ያላችሁ የክህሎት አበልጻጊዎች፣ አሳዳጊዎች እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይኽንን ፕሮጀክት እና እንቅስቃሴዎቹን እንዲደግፉ ጥሪ አቀርባለሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው “ውድ ባለተሰጥዖዎች፣ የኢትዮጵያችን ጥንካሬ በእናንተ እድገት ላይ የተመሠረተ ነው” ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!