
ባሕር ዳር: ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሻይ ቅጠል ምርት በቀጣይ በስፋት እንዲመረት ለማድረግ እንደሚሠራ የክልሉ ግብርና ቢሮ አሳዉቋል፡፡
የአፍሪካ የሻይ ቅጠል አምራቾች በዓለም ዓቀፍ የሻይ ገበያ ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በተለይ ኬንያ በዓለም በሦስተኛ ደረጃ ሻይ ቅጠልን በማምረት የተቀመጠች ሲኾን ምርቱን ወደ ዉጭ በመላክ ደግሞ አንደኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። እንደ ኬንያ የሻይ ቦርድ መረጃ እ.ኤ.አ በ2023 ሀገሪቱ ወደ ውጭ ከላከችው የሻይ ቅጠል ምርት 180 ቢሊዮን የኬንያ ሽልንግ ያገኘች ሲኾን ለሀገር ውስጥ ገበያ ካቀረበችው ደግሞ 16 ቢሊዮን ሽልንግ ገቢ አግኝታለች፡፡
ኢትዮጵያም ልክ እንደ ኬንያ ሁሉ ለሻይ ቅጠል ምርት ምቹ የኾነ የአየር ጸባይ እና የአፈር ኹኔታ ያላት ሀገር ናት፡፡ ይሁንና ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያመላክተው ባለፉት 11 ወራት 950 ቶን በአግባቡ የተዘጋጀ የሻይ ቅጠል ምርት ለውጭ ገበያ በመላክ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል። ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ50 ቶን ብልጫ ማሳየቱም ተጠቁሟል፡፡
እስካሁን ከሻይ ቅጠል የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ በዓመት ከ3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አይበልጥም፡፡ ታዲያ ሀገሪቱ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በሩዝና ሻይ ቅጠል ምርት ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ለመኾን እየሠራች ትገኛለች፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሻይ ቅጠልን በስፋት ለማምረት ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡
የአማራ ክልል ደግሞ ለማንኛውም ምርት ምቹ የኾነ የአየር ጸባይ እና የአፈር ሁኔታ ያለዉ መኾኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አመላክቷል፡፡ ክልሉ ሻይ ቅጠል ማምረት ላይ የሠራው ሥራ ምን ይመስላል? ስንል በቢሮው የአትክልት ፍራፍሬ እና መስኖ አጠቃቀም ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነውን ጠይቀናል፡፡
በክልሉ እስካሁን የሻይ ቅጠልን ለማምረት ቢሮዉ የሠራዉ ሥራ እንደሌለ ገልጸዉ ምርቱን በትላልቅ የእርሻ ቦታዎች ላይ የግል ባለሀብቶች ሊያመርቱ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ ይበልጣል አክለዉም በአማራ ክልል ለምርቱ ምቹ የአየር ንብረት እና የአፈር ኹኔታ በመኖሩ የዝናብ ስርጭት እጥረት ሊገጥም ቢችል እንኳን መስኖን ጭምር በመጠቀም ማምረት እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡
እስካሁን ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መኾኑን የገለጹት አቶ ይበልጣል ምርቱን በስፋት ለማምረት በምርምር የተደገፈ ሥራ መሠራት እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ በሠርቶ ማሳያዎች እና በችግኝ ጣቢያዎች ላይ የልምምድ ሥራዎችን በመሥራት፣ ለአርሶ አደሮች እና ለአምራች ባለሀብቶች ሥልጠናና ትምህርት በመስጠት፣ ቢሮው የምርቱን አዋጭነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ምርቱ በክልሉ እንዲመረት ለማድረግ ይሠራልም ብለዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!