“ዩኒቨርሲቲው ከ32 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን ለማኅበረሰቡ ሰጥቷል” የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አሥራት አፀደወይን (ዶ.ር)

12

ጎንደር: ነሐሴ 6/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ የመዝጊያ መርሐ ግብር አካሂዷል። ዩኒቨርሲቲው ባለፉት የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብሮችም 400 ሺህ የሀገር በቀል ችግኞችን ተክሏል ተብሏል።

በመዝጊያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ.ር) ከተተከሉት ችግኞች 67 በመቶ የሚኾኑትን ማጽደቅ ተችሏል ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ከጎንደር ከተማ አሥተዳደር ጋር በመተባበር ስድስት ሄክታር የተራቆተ መሬት እንዲያገግም በችግኝ መሸፈን ተችሏል ነው ያሉት።

በዘንድሮ ዓመት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ 12 ሺህ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል ያሉት ፕሬዚዳንቱ በሦስት ዙር 8 ሺህ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል። እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ቀሪ 4 ሺህ ችግኞች ዛሬ ይተከላሉ። ፕሬዚዳንቱ “ዩኒቨርሲቲው ካፈላቸው ችግኞች ውስጥ ከ32 ሺህ በላይ ሀገር በቀል ችግኞችን ለማኅበረሰቡ ሰጥቷል” ነው ያሉት።

የችግኞችን የፅድቀት መጠን ለመጨመር ውኃ የማጠጣት፣ የመኮትኮት እና መሰል የመንከባከብ ሥራዎች ይሠራሉም ነው ያሉት። ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ችግኝ ሲተክሉ አሚኮ ያገኛቸው አቶ ነጋ መስፍን እና ወይዘሮ ፈንታየ ብርሐን በቻሉት አቅም የተከሏቸው ችግኞች በተገቢው መንገድ እንዲፀድቁ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መኾኑን ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አዲስ ዓለማየሁ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሀገራዊ የግብርና ኢንቨስትመንት ፎረም ሊካሄድ ነው።
Next articleበአማራ ክልል ለሻይ ቅጠል ምርት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገለጸ፡፡