“በመመካከር እና በመወያየት የማይሽር ቁስል የለም” አምባሳደር መሐሙድ ድሪር

11

ባሕር ዳር: ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በድሬዳዋ ከተማ አሥተዳደር የአጀንዳ ማሠባሠብ የምክክር ምዕራፍ ዛሬ ተጀምሯል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር የፍቅር እና የሰላም ተምሳሌት የኾነችው ድሬዳዋ ስኬታማ የአጀንዳ ማሠባሠብ ሂደት እንደምታከናውን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የምክክር ሂደቱ ለኢትዮጵያ ተስፋን በማለምለም ችግሮችን ከግጭት ይልቅ በውይይት የመፍታት ባሕል የሚጎለብትበት መኾኑ ተገልጿል፡፡ ኮሚሽነሩ በውይይቱ የሚገደብ ሃሳብ እንደማይኖርም ገልጸዋል። መነጋገር እና መወያየት የችግሮች ሁሉ ብቸኛው መፍትሔ መኾኑን የተናገሩት ኮሚሸነሩ በጦርነት እና ግጭት የሚጠፋ ሕይወት እንዲሁም የሚወድም የሀገር ሃብት መፍትሔ ሊበጅለት ይገባልም ብለዋል።

“በመመካከር እና በመወያየት የማይሽር ቁስል የለም” ያሉት አምባሳደር መሐሙድ መነጋገርን እና መወያየትን ለቀጣዩ ትውልድ የምናስረክበው ወርቃማ ባሕል ሊኾን እንደሚገባ ጠቁመዋል። ተሳታፊዎች የአጀንዳ ማሠባሠብ መድረኩን ዓላማ በሚገባ በመረዳት ሰፊ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
በመድረኩ የተለያዩ የማኅበረሰብ ወኪሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሦስቱ የመንግሥት አካላት ወኪሎች፣ የተለያዩ ማኅበራት እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እየተሳተፉ ነው።

እንደ ኢቢሲ ዘገባ በአጀንዳ ማሠባሠብ የምክክር መድረኩ ክልላዊ እና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ሃሳቦች እና አጀንዳዎች ይነሳሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article26 ሕንዳውያንን የያዘ ነጻ የጤና አገልግሎት ሰጪዎች ቡድን ኢትዮጵያ ገባ።
Next articleሀገራዊ የግብርና ኢንቨስትመንት ፎረም ሊካሄድ ነው።