
ባሕር ዳር: ነሐሴ06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመጀመሪያው ዙር ዓለም አቀፍ የክረምት ነጻ የጤና አገልግሎት ሰጪዎች ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል። የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኅላፊዎች በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተገኝተው ለቡድኑ አቀባበል አድርገውለታል። ቡድኑ 26 ነጻ የጤና አገልግሎት ሰጪ ሕንዳውያንን የያዘ መኾኑን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ሕንዳውያኑ በሮተሪ ኢንተርናሽናል የአዲስ አበባ ክለብ፣ በሮተሪ ኢንተርነሽናል ቻንዲጋር ክለብ እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ትብብር መምጣታቸው ተገልጿል። የጤና አገልግሎት ሰጪ ቡድኑ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፣ በአለርት ሆስፒታል እና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከ1 ሺህ 500 በላይ ነጻ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።
የክረምት በጎ አድራጎት አካል የኾነው ነጻ የጤና ምርመራ እና ሕክምና አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም የጤና ተቋማት መጀመሩ ይታወቃል። እንደ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ ከተለያዩ ሀገራት የክረምት ነጻ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የተለያዩ ሀገር ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መኾኑን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!