
ባሕር ዳር: ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት የሥራ እንቅስቃሴ ያለበትን ደረጃ ተመልክተዋል። “ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት የውኃ አቅርቦት ያስፈልጋል” ያሉት ሚኒስትሩ የመገጭን ግድብ በፍጥነት በማጠናቀቅ የጎንደርን የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር ለመፍታት ርብርብ እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በፕሮጀክቱ ያለውን የሰው ኃይል ስምሪት፣ ማሽነሪዎች፣ ያሉትን ግብዓቶች እና የሥራ እንቅስቃሴዎችን ተመልክተዋል። ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ የክልሉ መንግሥት፣ የከተማ አሥተዳደሩ እና የኅብረተሰቡ ድጋፍ አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል ።
በጉብኝቱ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኃላን ጨምሮ የከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል። የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት 185 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የመያዝ አቅም እንዳለው ከጎንደር የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!