
ደሴ: ነሐሴ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ከ44 ሺህ በላይ ከሚኾኑ ግብር ከፋዮች ግብር ለመሰብሰብ በእቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው። ከዚህ ውስጥም እስካሁን 85 በመቶ የሚኾኑት የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ ከፍለው አጠናቅቀዋል።
በዞኑ ግብር መክፈል ላይ ምሳሌ የሚኾኑ በርካታ ግለሰቦች ይገኛሉ። ከዚህ ውስጥ ደግሞ በወረባቡ ወረዳ ቢስቲማ ከተማ ነዋሪ የኾኑት ግብር ከፋይ ይገኙበታል። ግብር ከፋዩ ከ1996 ጀምሮ ከሚያገኙት ገቢ የተጣለባቸውን ግብር እየከፈሉ እንደሚገኙ ነው ለአሚኮ የገለጹት።
ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታ መኾኑን ያነሱት ግብር ከፋዩ አሁን ላይም ከምግብ ቤት፣ ከወፍጮ አገልግሎት እና ከተከራይ አከራይ ከሚያገኙት ገቢ የሚጠበቅባቸውን ከ45 ሺህ ብር በላይ ግብር ከፍለዋል። የማኅበረሰቡን የልማት ጥያቄ ለማሟላት ግብር መሠረታዊ ጉዳይ በመኾኑ ዜጎች ከሚያገኙት ገቢ ተመጣጣኝ ግብር ሊከፍሉ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ አሕመድ ሙሐመድ እንዳሉት በዞኑ ግብር ይከፍላሉ ተብሎ ከታቀደው 44 ሺህ 554 የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋይ እስከ ነሐሴ 02/2016 ዓ.ም 85 በመቶ መክፈል ችለዋል። ይሠበሠባል ተብሎ ከታቀደው 325 ሚሊዮን ብር ውስጥ 71 ነጥብ 4 በመቶ ገቢ መሠብሠብም ተችሏል።
ቅሬታ እና ይግባኝ የጠየቁ ግብር ከፋዮች ጉዳይ በሂደት ላይ መኾኑንም አስረድተዋል፡፡ በአንድ ጊዜ መክፈል የማይችሉ ግብር ከፋዮች በሦስት ጊዜ ክፍያ እንዲከፍሉ መደረጉ ለታቀደው ግብር መሠብሠብ አለመሳካት በምክንያትነት ተቀምጧል። በዞኑ ግብር መሠብሠብ ከተጀመረባቸው 28 ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ውስጥ በ15ቱ ማጠናቀቅ ተችሏል።
በቀሪዎቹ ወረዳዎች ወቅቱን እና የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ግብር ከፋዮች እስከ ነሐሴ 10/2016 ዓ.ም ባለው ጊዜ እንዲያጠናቅቁ ዕድል ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል። ከነሐሴ 10/2016 ዓ.ም በኋላ ቅጣት እና ወለድን ጨምሮ እንዲከፈል ይደረጋል ብለዋል። ይህ እንዳይኾን ተጨማሪ የመክፈያ ጣብያዎችን ጭምር በማቋቋም የመሠብሠብ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ግብር ለአንድ ሀገር የልማት መሠረት በመኾኑ ማኅበረሰቡ የተጣለበትን ግብር በወቅቱ እንዲከፍል ጠይቀዋል። የታቀደው ዕቅድ እንዲሳካ እና በቀጣይም የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር በተቀመጠው ጊዜ እንዲጠናቀቅ ተቋማት አጋዥ ኾነው እንዲሠሩም ኀላፊው መልእክት አስተላልፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!