
ደሴ: ነሐሴ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሁሉን አቀፍ ልማትን ለማረጋገጥ መንግሥት ያካሄደውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ሰበብ በማድረግ በኮምቦልቻ ከተማ በተለያዩ እቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ነዋሪዎች ተናግረዋል። የዋጋ ጭማሪውን ለማረጋጋት የከተማ አሥተዳደሩ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። የተወሰደው እርምጃ አግባብነት ያለው መኾኑን የገለጹት አሚኮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች የእቃዎች ዋጋ ወደነበረበት መመለሱን ገልጸዋል።
ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በመተባበር የገበያ ማረጋጋቱ ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ የሚገኙ ነጋዴዎች እቃዎችን ያለአግባብ በሚደብቁ ነጋዴዎች ላይ መንግሥት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል። የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ዮናስ መላኩ የዋጋ ጭማሪ እና የምርት መደበቅ ተግባር ላይ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየወሰዱ ገበያውን ለማረጋጋት እየሠሩ መኾኑን አንስተዋል።
የገበያ ማረጋጋት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት አቶ ዩናስ ኅብረተሰቡ የምርት እጥረት የሌለ መኾኑን ተገንዝቦ በተረጋጋ መልኩ ግብይቱን እንዲያከናውን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ አበሻ አንለይ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!