የኮሌራ በሽታን ለመከላከል ከአጋር ተቋማት በጋር እየሠራን መኾኑን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ።

20

ባሕር ዳር: ነሐሴ 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የኮሌራ እና የወባ በሽታ መከሰቱን ተከትሎ የዞኑ ጤና መምሪያ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩም የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኅላፊ ልዑል ሀጎስ፣ የዞኑ ጤና መምሪያ ምክትል ኅላፊ ስማቸው ግዳይ እንዲሁም ሌሎች የዞን፣ የወረዳ እና ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኅላፊዎች ተገኝተዋል።

የዞኑ ጤና መምሪያ ምክትል ኅላፊ ስማቸው ግደይ ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም በቃብትያ ሁመራ ወረዳ አደባይ ቀበሌ በተደረገ ምርመራ በሽታው መከሰቱ እንደተረጋገጠ ጠቁመው እስከዚህ ሰዓት ድረስ 55 ሰዎች በበሽታው እንደተጠቁ እና የሦስት ሰዎች ሕይዎት እንዳለፈ ተናግረዋል።

የበሽታው ምልክት ተቅማጥ፣ ማስመለስ፣ የአፍ መድረቅ፣ የቆዳ መሸብሸብ እና ከመጠን በላይ የውኃ ጥማት መኾናቸውን ያስረዱት ምክትል ኅላፊው ማንኛውም ሰው እነዚህን ምልክቶች ሲያይ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ጤና ተቋም መሄድ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ዞኑ የተለያዩ የማኀበረሰብ ክፍሎች ለልማት እና ማኀበራዊ መሥተጋብሮች የሚመጡበት መኾኑ ለብሽታው ሥርጭት ምቹ አጋጣሚ ስለሚፈጥር ልዩ ትኩረት በመስጠት በርብርብ የሥርጭት መጠኑን ለመቀነስ ልንሠራ ይገባል ብለዋል።

የልማት ቀጣናዎች፣ የፀበል ቦታዎች፣ የተፈናቃይ ማቆያ ቦታዎች፣ ማረሚያ ቤቶች ለበሽታው የበለጠ ተጋላጮች መኾናቸውን ጠቅሰዋል።

ንፅህናውን የጠበቀ ውኃ መጠቀም፣ ምግብን አብስሎ መመገብ፣ መፀዳጃ ቤቶችን በአግባቡ መጠቀም፣ የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ እና እጅን በወሳኝ ወቅቶች በሳሙና በመታጠብ በሽታውን መከላከል እንደሚገባም ተናግረዋል።

ሌላው የወቅቱ አንዱ ወረርሽኝ የኾነው የወባ በሽታ በዞኑ ትኩረት የሚያስፈልገው መኾኑንም አንስተዋል። በዞኑ ከ83 ሺህ በላይ ሰዎች የወባ ተጠቂ እንደነበሩ ጠቅሰው በበሽታው የሦስት ሰዎች ሕይወት እንዳለፈም ገልጸዋል።

ወቅቱን ጠብቅው የሚከሰቱ ተላላፊ በሽታዎችን መከላከል የጤና ተቋማት ዋናኛ ተልዕኮ ቢኾንም ሌሎች ተቋማትም ርብርብ ማድረግ አለብን ያሉት የዞኑ የብልፅግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኅላፊ ልዑል ሀጎስ የኮሌራ በሽታ ሥርጭትን መከላከል የሁላችንም ድርሻ ሊኾን ይገባል ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች የበሽታው ምልክት ከታየበት ጊዜ አንስቶ ለኀብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራን ሲሰሩ እንደነበር አንስተው አሁንም በሽታው እንዳይስፍፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

እንደ ዞኑ ኮሙኒኬሽን ዘገባ የመድረኩ ተሳታፊዎች በጤና ተቋማት የተለያዩ የግብዓት እጥረቶች መኖራቸውን አንስተው ይኽም የኮሌራ በሽታን በቀላሉ ለመከላከል እንቅፍት እንደሚኾንባቸው በመግለጽ መንግሥት እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ግብዓቶችን ተደራሽ እንዲያደርጉላቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአሸንድየ እና የሶለል በዓላትን በድምቀት ለማክብር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን የሰሜን ወሎ ዞን አስታወቀ፡፡
Next articleምሥጋና