
ባሕር ዳር: ነሐሴ 5/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአሸንድየ እና የሶለል በዓላትን በድምቀት ለማክብር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን የሰሜን ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል አሸንድየ በሰሜን ወሎ እና ሻደይ በዋግኽምራ በድምቀት ይከበራሉ፡፡
በዓላቱ የቀደመ ታሪክ፣ ባሕል፣ እሴት እና ሃይማኖት የሚገለጽባቸው ናቸው፡፡
የወርሐ ነሐሴ ጌጦቹ የኾኑት እነዚህ በዓላት ዓመት አልፎ የሚከበሩበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ይናፈቃሉ፡፡
ጎብኚዎችን በመሳብ፣ የሀገርን ባሕል እና ወግ ለዓለም በማስተዋወቅ ታላቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡
የሰሜን ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ገነት ሙሉጌታ አሸንድዬ እና ሶለል ከጥንት ዘመን ጀምረው የመጡ የሕዝብ በዓላት መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ የኾኑት እነዚህ በዓላት የልጃገረዶች የነጻነት መገለጫ በዓላት ናቸውም ብለዋል፡፡
በዓላቱ ለሀገር እና ለሕዝብ ታላቅ ፋይዳ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
በዓላቱ ሕዝብ ሃይማኖት እና ባሕሉን የሚያስተዋውቅበት ናቸው ብለዋል፡፡
ሕዝባዊ መሠረት ያላቸው ጥንታዊ በዓላቱ ሕዝቡ የኔ ናቸው ብሎ ሲጠብቃቸው እና ሲያከብራቸው የቆዬ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡
የጎብኚዎችን ትኩረት በመሳብ የአማራ ክልልን ገጽታ የሚያሳዩ ድንቅ ሃብቶች መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በዓላቱን ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡
በዓላቱ ታሪካቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ የታቀዱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንደሚያስፈልጉም አንስተዋል፡፡
በዓሉን ለማክበር ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ቱሪዝም መምሪያው በዓላቱን በተገቢው መንገድ ለማክበር ወልድያ ዪኒቨርሲቲን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን የተናገሩት ኀላፊዋ ሕዝባዊ በዓላቱ ታሪካቸውን ጠብቀው በሰላም እንዲከበሩ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዓላቱ የሕዝብ መገለጫዎች በመኾናቸው የእኔ ናቸው ብሎ መጠበቅ ይገባልም ብለዋል፡፡
ትውፊታቸውን ጠብቀው እንዲሸጋገሩ ማኅበረሰቡ የሚጠበቅበትን አደራ እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡
ቱሪዝም መምሪያ በዓላቱን በድምቀት ለማክበር የሚያደርገውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!