የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ከ400 በላይ ቤቶችን በመገንባት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸዉ የማኀበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ ገለጸ።

26

ደብረ ብርሃን: ነሐሴ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከተማ አሥተዳደሩ ለዚሁ ተግባር 5 ሚሊየን ብር በመመደብ ከኢንዱስትሪዎች እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
እስካሁንም 180 ቤቶችን በማደስ እና በአዲስ በመገንባት ለተጠቃሚዎች ማስተላለፉን አስታውቋል፡፡

በጀርመን ከሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተገኘ የ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በእምየ ምኒልክ ክፍለ ከተማ የ14 አባወራዎች ቤት ግንባታ ተጀምሯል።

የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ከተማ አሥተዳደሩ በሰው ተኮር የልማት እንቅስቃሴ የተሻለ ልምድ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

አሥተዳደሩ ከዚህ ቀደምም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች ቤት በመገንባት ማስረከቡን አስታውሰዋል፡፡
በቀጣይም ከተለያዩ አማራጮች በሚገኝ ሀብት የገቢ አቅምን መሰረት ያደረገ እገዛ እንደሚቀጥል ከንቲባ በድሉ ተናግረዋል፡፡

የከተማ አሥተዳደሩ ሴቶች፣ ህፃናት እና ማኀበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኅላፊ በለጥሽ ግርማ በክረምት ወቅት የሚሠሩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ዉጤታማ እንዲኾኑ ከማኀበረሰቡ ጋር በመቀናጀት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የቤት ግንባታዎቹ በ60 ቀናት ዉስጥ ተጠናቅቀው ለተጠቃሚዎች ርክክብ ይደረጋልም ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ብርቱካን ማሞ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የተከዜን ጎርፍ ከላይ ወደታች እያየን ለመራመድ በመብቃታችን ተደስተናል” የዝቋላ እና ስሃላ ሰየምት ወረዳ ነዋሪዎች
Next articleየአሸንድየ እና የሶለል በዓላትን በድምቀት ለማክብር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን የሰሜን ወሎ ዞን አስታወቀ፡፡