
ሰቆጣ: ነሐሴ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የዝቋላ እና ስሃላ ሰየምት ወረዳን የሚያገናኘው የተከዜ የብረት ድልድይ ነሃሴ 7/2012 ዓ.ም በከባድ ጎርፍ ምክንያት ተደርምሷል። ባለፉት አራት ዓመታትም የአካባቢው ሕዝቦች ለከፋ ችግር ሲጋለጡ መቆየታቸውን ይገልጻሉ።
ቄስ ኪሮስ ፈንታየ የተከዜ ወንዝን ተጠልለው የሚኖሩ የዝቋላ ወረዳ ነዋሪ ሲኾኑ በድልድዩ መፍረስ ምክንያት የሞተር ጀልባቸው ሽንኩርት እንደተጫነ ለጎርፍ ሲሳይ እንደኾነባቸው ያስተውሳሉ። በርካታ ሰዎችም ለአዞ እራት ኾነው እንደቀሩ የገለጹት ቄስ ኪሮስ የድልድዩ መልሶ መገንባት “የተከዜን ጎርፍ ከላይ ወደታች እያየን ለመራመድ በመብቃታችን ተደስተናል” ብለዋል።
በሰሃላ ሰየምት ማዶ ተከዜ ዳር የሚኖሩት አቶ ታፈረ እማኙ በበኩላቸው የተከዜ ድልድይ ከተደረመሰ ጀምሮ መከራችን በዝቶ መንግሥትም የረሳን መስሎን ነበር ብለዋል። በቅርቡ በጀልባ የተገለበጡት ሰዎች ሞት አንዱ የመከራችን ማሳያ ነው ያሉት አቶ ታፈረ በየዓመቱ የምንገብራቸው ሰዎች ቁጥር በረካታ ነው ብለዋል። ድልድዩ ሳልሞት ተጠናቅቆ በማየቴ ደስተኛ ነኝ ሲሉ አክለው ገልጸዋል።
የሰሃላ ሰየምት ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ ሲሣይ ብሩ ድልድዩ በመጠናቀቁ መደሰታቸውን ገልጸው ለዚህም ከፍተኛ ዋጋ ለከፈሉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።ነገር ግን ቀላል መኪናዎችን እና እስከሎዳቸው ከ20ቶን በላይ የማይጭኑ ተሽከርካሪዎች ማለፍ አይችሉም መባሉ እንዳስከፋቸው አልደበቁም። በቀጣይም ማጠናከሪያ ግንባታ እንዲደረግበት አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል አቶ ሲሣይ ብሩ።
የተከዜ ብረት ድልድይ መጠናቀቅ የሁለቱን ወረዳዎች ትብብር የበለጠ ያጠናክራል ያሉት የዝቋላ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ እና ምክትል አሥተዳዳሪ እስጢፋኖስ ወንዳዬ ለዚህ ደረጃ ላደረሱት አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የስሃላሰየምት ወረዳን ሕዝብ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ መቀመጫ የሚያገናኘው የተከዜ የብረት ድልድይ 146 ሜትር ርዝመት ያለው መኾኑን ገልጸዋል። በምክትል አሥተዳዳሪ ደረጃ የመንገድ መምሪያ ኅላፊ ፀጋው እሸቴ በፌደራሉ እና በክልሉ መንግሥት ከ350 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበት ተናግረዋል።
የተከዜ ወንዝ የብረት ድልድይ በጊዜያዊነት ተሠርቶ እንዲጠናቀቅ ድጋፍ ላደረጉት የፌደራል መንገዶች አሥተዳደር፣ የክልሉ መንግሥት እና የወረዳው ሕዝብ ምስጋና ያቀረቡት አቶ ፀጋው፣ ዘለቄታዊ መፍትሔ ያለው የኮንክሪት ድልድይ እንዲሠራ ለፌደራሉ መንግሥት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
የመንገዶች አሥተዳደር የድልድይ እና ስትራክቸር ሥራዎች ዳይሬክተር ኢንጅነር ጌትነት ዘለቀ በድልድዩ 20ቶን ክብደት ያላቸው ተሽከርካሪዎች፣ ቀላል መኪናዎችም ተደርበው ማለፍ እንደሌለባቸው አሳስበዋል። ይህ የኾነበት ምክንያት ድልድዩ ከምሰሶ እስከ ምሰሶ 60 ሜትር ርዝመት ያለው በመኾኑ ነው ብለዋል።
የድልድዩ አማካይ የአገልግሎት ዘመን ከ12 እስከ 15 ዓመት ነው ያሉት ኢንጅነር ጌትነት ዘለቀ በቀጣይ ዓመት በበጋ ወቅት የማጠናከሪያ ብረት እና ምሰሶ ከተገጠመለት በኃላ ወደ 40 ቶን ከፍ ለማድረግ እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!