
ባሕር ዳር: ነሐሴ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ስለ ለውጥ እና የለውጥ ፍራቻችን እንዳነሳ ያደረገኝ ከሰሞነኛው የሀገራችን ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ የማኅበረሰቡን ስጋት ተመልክቼ ነው። የዘርፉ ባለሙያ ስላልኾንኩ በፖሊሲው ላይ ሃሳብ ለመሥጠት አልችልም። ግን ስለ ለውጥ ያለን አስተሳሰብ ላይ የራሴን ትዝብት ለማጋራት ስለወደድኩ ነው።
በሀገራችን በ1997 ዓ.ም በነበረው ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀሳብ ትግል አስኳል ከነበሩት ጉዳዮች መካከል አንዱ የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ እንደነበር አስታውሳለሁ።
የያኔው ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ የነጻ ገበያ ሥርዓትን ለጊዜው ለኢትዮጵያ ጠቃሚ እንዳልኾነ እና የመንግሥት በተመረጡ ዘርፎች ላይ ጣልቃ መግባትን ሲያቀነቅን፣ አብዛኛው በተቃዋሚ ጎራ የነበረው ፖለቲከኛ እና ምሁር የነጻ ገበያ ሥርዓትን ያቀነቅን እንደነበር አስታውሳለሁ።
ለሁሉም ጊዜ አለው እና ዛሬ ላይ ያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የታገሉለት፣ በርካታ ሕዝብም ሃሳባቸውን ደግፎ የቆመለት ፖሊሲ ሊተገበር ነው ሲባል ምን ያህል እንዳሰጋን እያየነው ነው። ይህንን ሃሳብ ለማንሳት የፈለግሁት የለውጥ ፍርሃታችን ለማሳየት እንጂ የነጻ ገበያ ሥርዓትን እና የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያን ለመደገፍም፣ ለመንቀፍም አይደለም።
እንደ ማኅበረሰብ ”ካልለመዱት መልዓክ የለመዱት ሰይጣን ይሻላል” የሚሉ ሥነ ቃሎች ያሉን ሕዝቦች እንደመኾናችን መጠን አዲስ ለውጥ ቢያስፈራን የሚገርም አይደለም። ከችግር ወጥተን የተሻለ ሕይወት ለመምራት ብንጓጓሞ አዲሱ መንገድ የሚያመጣው መውደቅ እና መነሳት ያሰጋናል። እናም ”ጎመን በጤና” አይነት አስተሳሰብ ስናራምድ እንስተዋላለን።
ለውጥን በመሻት እና በመረዳት አሮጌውን ትተው በአዲስ መንገድ ሕይወትን ለመቃኘት የሚሞክሩትንም የምናወጣላቸው ስም አናጣም። በግለሰብ ደረጃ አዲስ ነገር የሚጀምሩትን ሰዎች በንቀት እና በስላቅ ማየት የተለመደ ተግባራችን እንደኾነ እታዘባለሁ።
እንደ ማኀበረሰብ አጥብቀን ከምንፈራቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ ለውጥን እና የተለየ ነገርን መሞከር ይመስለኛል። ከከተማ እስከ ገጠር፣ ከምሁር እስከ አርሶ አደር የቆየውን የሕይወት ዘይቤ ማስቀጠል ይቀናናል። ይህ የኾነበት ምክንያት ደግሞ የባሕል እና የልማድ እስረኛ በመኾናችን ይመስለኛል። የቆየውን ዘመን ስንናፍቅ ዘመኑን የሚመጥን ሕይወት ባለመከተላችን በችግር እየተጠበስን ነው። ዘመኑ የመለወጡን እውነት መረዳት እና መቀበል ሲያቅተንም እየታዘብን ነው።
ገበሬው አብዛኞቹን የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓቶች እና አሠራሮች አሁን ድረስ ለመቀበል ሲቸገር እናያለን። በጊዜ አጠቃቀም፣ በጤና አጠባበቅ፣ በቁጠባ፣ በጾታ እኩልነት እና በሌሎችም ጉዳዮች አሁን ድረስ አዳዲስ አስተሳሰቦችን ለመቀበል ስንቸገር ይስተዋላል።
አብዛኛው የከተማው ማኀበረሰብም ጊዜውን የሚመጥን አስተሳሰብ እና ተግባር ላይ ነው ብሎ ማሰብ ይከብዳል። የጽዳት አጠባበቁን እንኳን ብንመለከት ብዙ ችግሮችን እናስተውላለን። በቢሮ መጸዳጃ ቤቶች፣ በሕዝብ መጸዳጃ ቦታዎች፣ በመዝናኛ ቦታዎች እንዲሁም በልዩ ልዩ ጎዳናዎች ጽዳት እና ንጽህናውን የሚጠበቀበትን መንገድ ስናይ ብዙ የሚያስተዛዝቡ ተግባሮችን እያየን ነው።
የመንግሥት ሠራተኛውም አሁን ድረስ የሕዝብ አገልጋይ ነኝ ብሎ የሚሠራ ስንት ነው?። በመስሪያ ቤቶች አዳዲስ አሠራሮች ሲመጡ ለአዲስ አስተሳሰብ ቅን ያለመኾን አዝማሚያ ይስተዋላል። ለዚህ ማሳያም ቢ. ፒ. አር፣ ቢ. ኤስ. ሲ፣ ካይዘን፣ የመሳሰሉት አዳዲስ የአሠራር እሳቤዎችን ያስተናገድንበትን አግባብ ማስተዋል እንችላለን። የተሻለ ውጤትን ለማምጣት የሚታለፍበትን የለውጥ ጎዳና እንፈራለን።
የዘመኑን ቴክኖሎጂ ማደግ፣ የሕዝብ ብዛት፣ የሀብት እጥረት እንዲሁም የውድድር ዘመን መኾኑን ግምት ውስጥ በማስገባት በግላችንም እንደ ማኅበረሰብም አዲስ ለውጥን የመከተል እና የመላመድ ባሕላችን ደካማ ኾኖ ይታየኛል። ሥራ አይናቅም እያልን የምናወራው ብዙዎቻችን ብንኾንም ያለንን አነስተኛ ገቢ በተጨማሪ ሥራ ለመደጎም የምንሠራው ስንቶቻችን ነን? እንደምናወራው ከውስጥ የተዋጠልን አይመስልም።
አንዳንዶች ለውጥን ለመቀበል የመፍራታችን ምክንያት አለመማር ነው ይላሉ። መማር የሚያመጣውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ባምንም፣ ችግሩ አለመማር ብቻ ግን አይመስለኝም። ለምሳሌ በጤናው ዘርፍ የጤና መድህን አተገባበርን እንመልከት። የጤና መድኅን አገልግሎትን ባህል በማድረግ እንደ ማኅበረሰብ የጤና ዋስትናውን ከማረጋገጥ ይልቅ በሰበብ አስባቡ ከአገልግሎቱ ሲርቅ የሚታየው የተማረ የሚባለው የኅብረተሰብ ክፍል ነው።
የሀገር ውስጥ ምርትን በመጠቀም፣ የቁጠባ ባሕልን በማዳበር፣ የቀጠሮ እና የሥራ ሰዓት በማክበር እና በሌሎችን መገለጫዎች የተማረ የሚባለው ማኀበረሰብ አልተማረም ከሚባለው ማኅበረሰብ ትርጉም ያለው ልዩነት አያሳይም። በየዓመቱ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ እና የኮሌጅ ምሩቃን መቀጠርን እንጂ ሥራ መፍጠርን ደፍረው ሲገቡበት አይስተዋልም። በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የአማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ‘ድሀ’ ወጣቶችን ሥራ እንዲፈጥሩ ለሦስት ወራት በግንበኝነት እና አናጺነት ሲያሠለጥናቸው የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ”የመንግሥት ሠራተኛ” ነበር። እነዚያ ወጣቶች ዛሬ አንቱ የተባሉ የሀገር ባለሃብት ሲኾኑ ያ ”የመንግሥት ሠራተኛ” ግን ዛሬም ድሀ የመንግሥት ሠራተኛ ነው። ይህ የሚያሳየው ለውጥን ከሩቅ እንፈራዋልን፤ ወይ ለለውጥ እያነበነብን አንተገብርም።
መቀየር የሌለባቸው አንዳንድ ባሕል እና እሴቶች ቢኖሩንም መሻሻልም ጭራሽ መቅረትም ያለባቸው የአኗኗር፣ የሕይወት፣ የችግር አፈታት ዘይቤዎችም እንዳሉ ይሰማኛል። መውደቅ እና መነሳትን መልመድ እና በፈተና አልፎ ለውጤት መብቃትን ባሕል ማድረግ ያስፈልገናል። ለውጥን ስናስብ አስቀድሞ ሆዳችን ባር ባር የሚለውን ሥነ ልቦና መፈተሽ እና ማስተካከል አለብን።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!