👉የቱሪዝም አባት

40

ባሕር ዳር: ነሐሴ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ኃብተሥላሴ ታፈሰ ይባላሉ። በ1918 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ነው የተወለዱት፡፡ በሕጻንነታቸው አባታቸው የጠረፍ አካባቢ አሥተዳዳሪ ኾነው ለሥራ ሲመደቡ ልጃቸውን ይዘው ለመሄድ ተቸገሩ፡፡ ታዲያ አውጥተው እና አውርደው ጎረቤታቸው የነበሩት የውጭ ሀገር ጥንዶች ሩሲያዊት ሚስት እና ግሪካዊ ባል ሕጻኑን ኃብተሥላሴን እየተንከባከቡ እንዲጠብቁላቸው በአደራ ሰጥተዋቸው ወደተመደቡበት ሥራ አቀኑ። እነዚህ የውጭ ሀገር ዜጎችም ሕጻኑን በደስታ ተቀብለው በጥሩ ሁኔታ እያሳደጉት በነበረበት ወቅት ፋሺስት ጣልያን ኢትዮጵያን ወረረች፡፡ በዚህ ምክንያት የኃብተሥላሤ አሳዳጊዎች ይዘውት ወደ ግሪክ ሄዱ። ሕጻኑ ኃብተሥላሴም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ግሪክ አቴንስ ከተማ ውስጥ ተማሩ።

ብዙም ሳይቆይ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተቀስቅሶ ግሪክ በፋሺስት ጣልያን እና በናዚ ጀርመን መዳፍ ሥር ወደቀች። በዚያ የመከራ ዘመን ላይም ባለአደራዎቹ ኃብተሥላሴን ከልጆቻቸው እኩል እየተንከባከቡ ማሳደጉን ቀጠሉበት።
በዚህ መካከል በስደት አውሮፓ የነበሩት የኃብተሥላሴ አባት ልጃቸውን በቀይ መስቀል በኩል አፈላልገው በማግኘታቸው ወደ እናት ሀገራቸው ተመልሰው መጡ። በትምህርት ረገድ ኃብተሥላሴ በግብጽ የቪክቶሪያ ኮሌጅ ለሁለት ዓመታት ተምረዋል። እ.ኤ.አ 1950 ወደ አሜሪካን ሀገር ሄደውም ከካርልቶን ኮሌጅ ሚኔሶታ በኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ እና በሥነ-መንግሥት አሥተዳደር በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡

ኃብተሥላሤ ሥራ የጀመሩት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ነበር። በዚሁ እየሠሩም በወቅቱ የሥራ ሚኒስትር የነበሩት ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ከወጣቱ ኃብተሥላሴ ጋር ለሥራ ጉብኝት ወደ አውሮፓ ተጓዙ። በአውሮፓ ቆይታቸው በተለያዩ ሀገራት የቱሪዝም ዘርፍ ተደነቁ፡፡ ኢትዮጵያ በቱሪስቶች ዘንድ ተወዳጅ ሊኾኑ የሚችሉ በርካታ ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ሃብቶች ባለቤት እንደኾነች እና በዘርፉ ጠንክሮ መሥራት ከተቻለ ብዙ ሃብት ማፍራት እንደሚቻል ኃብተሥላሴ ተገነዘቡ፡፡

ከአውሮፓ እንደተመለሱም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ እንዲያቋቁሙ በንጉሠ ነገሥቱ በመታዘዛቸው ቱሪዝም ላይ መሥራት ጀመሩ፡፡ ከሥራቸው መካከል እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ የቱሪዝም መለያ ኾኖ ያገለገለው “ኢትዮጵያ! የ13 ወር ፀጋ ” Ethiopia: Land of 13 Months of Sunshine” የኃብተሥላሴ የምናብ ውጤት ነው።

የኢትዮጵያ ቅርስ እና ታሪክ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ሰፊ ዕውቅና እንዲያገኝ መሠረት ያኖሩም እሳቸው ናቸው፡፡ የጢስ ዓባይ፣ ጣና፣ ጎንደር፣ ላሊበላ እና አክሱም የጎብኝት መሥመር እንዲዘረጋ እና በዓለም እንዲታወቅ ያደረጉም እሳቸው ናቸው፡፡

በርካታ ቋንቋዎችን የሚናገሩት ኃብተሥላሴ ከቱሪዝም ተግባራቸው በተጨማሪ የልዑል መኮንን ኃይለሥላሴ መታሰቢያ የኾነው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንዲከፈት ያደረጉም ሰው ናቸው፡፡
በውጭ ሀገራት የንግድ ትርኢቶች ላይ የኢትዮጵያን እጹብ ድንቅ ቁሳቁስ በመያዝ ኢትዮጵያን በማስተዋወቁ ረገድ በርካታ ሥራዎችን አከናውነዋል።
የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅትንም አቋቁመዋል፡፡ ይህ ድርጅት የሀገሪቱን ቅርስ እና ባሕል ከማስተዋወቁ በተጨማሪ ብዙ ትርፍ የሚያስገኝ ተቋም ኾኗል።

የእሳቸው አሻራ ካረፈባቸው ፕሮጀክቶች መካከል የሒልተን ሆቴል፣ የኢትዮጵያ ምግብ ኢንስቲትዩት፣ ሀገርን ለማስተዋወቅ ሥራ ላይ የዋሉ አያሌ ንድፎች እና መጽሔቶች ተጠቃሽ ናቸው። በሥራቸውም በብዙዎች ዘንድ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ መሥራች በመባል ይታወቃሉ ሲል ቱሪዝም ዶት ኮም አሰነብቧል፡፡

አቶ ኃብተሥላሴ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ አብቦ እንዲያፈራ ላከናወኗቸው ወርቃማ ተግባራትም የገንዘብ፣ የዋንጫ እና የወርቅ ሽልማት ከኢትዮጵያ መንግሥት ተበርክቶላቸዋል። በተጨማሪም በቅርስ እና ባሕል ዘርፍ የ2007 ዓ.ም ‹‹የበጎ ሰው ሽልማት›› ተሸላሚም ኾነዋል። የአንድ ሴት እና የሁለት ወንዶች ልጆች አባት የኾኑት‹‹የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ አባት›› አቶ ኃብተሥላሴ ታፈሰ ነሐሴ ሦስት ቀን 2009 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት፡፡

👉 የአፍሪካ ዓመት

17 የአፍሪካ ሀገራት ከአውሮፓ የቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነጻ የተላቀቁት እ.ኤ.አ 1960 ነበር፡፡ ታዲያ ይህ ዓመት ‘የአፍሪካ ዓመት’ በመባል ይጠራል፡፡
በተለይ በነሐሴ ወር ከዘጠኝ በላይ የኾኑ የአፍሪካ ሀገራት የነፃነት በዓላቸውን አክብረዋል፡፡
ነሐሴ 1 ቀን 1960 ቤኒን ለ60 ዓመታት አሳር ስቃይ ያበላትን የፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ማክተሙን አበሰረች።

ከሁለት ዓመታት በፊት በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ መሠረትም ነፃነቷን ከፈረንሳይ እጅ ስትረከብ ስሟን ዳሆሜ የሚል ነበር፡፡
ሀገሪቱ ሁበርት ማጋንን የመጀሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት በማድረግ ነፃነቷን ጀምራለች። ቤኒን የተባለችው ደግሞ ከ1975 በኋላ መኾኑን የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ።
ኒጀር የፈረንሳይ ወራሪዎችን ላለማስገባት በጀግንነት ከተከላከሉ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት አንዷ ናት። ይሁን እንጂ ቆራጥ ትግሏ ወራሪዎችን ቢያዘገያቸውም ፈጽሞ ግን አላቆማቸውም። እናም ከ1883 ጀምሮ በፈረንሳይ ሥር ኾና ቆይታለች፡፡

‘ኢንሳይክሎፒዲያ ኦፍ አፍሪካን ሂስትሪ’ በተሰኘ የታሪክ ሰነድ ላይ እንደተቀመጠው ነሐሴ 3 ቀን 1960 ኒጀር ሌላዋ ነጻነቷን ያወጀች ሀገር ኾናለች።
ሐማኒ ዲዮሪ የተባለ የሀገሯን ልጅ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንቷ አድርጋም በመሾም ነጻነቷን አውጃም ነበር። ፕሬዚዳንት ሐማኒ ለ14 ዓመታት ኒጀርን መርተዋል፡፡

በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስትማቅቅ የቆየችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ቡርኪ ናፋሶም ነጻነቷን ያወጀችው ነሐሴ 5 ቀን 1960 ነበር፡፡
ማውሪስ ያሚዮጎ የመጀመሪያ ጥቁር የቡርኪ ናፋሶዎቹ ፕሬዚዳንት ኾነው መመረጣቸው ይታዎሳል፡፡ ስድስት ዓመታትም ሀገሪቱን አሥተዳድረዋል።

በ1984 ሥልጣን ላይ የወጡት ወጣቱ አብዮተኛ መሪ ቶማስ ሳንካራ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በሥር ነቀል እርምጃዎች የሕዝቡን ሕይወት መቀየር ችለዋል፡፡ ለቡርኪ ናፋሶ ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካ መኩሪያ የኾኑ ድንቅ መሪም ነበሩ።
አይቮሪ ኮስትም ነጻነቷን የተጎናጸፈችው በነሐሴ ወር ነበር፡፡ ሀገሪቱ ፊሊክስ ሀውፌት የመጀመሪያ ፕሬዚዳንቷ አድርጋ በመሾም ደማቅ ታሪክ ጽፋለች። ፍራንኮይስ ቶምበልባየ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚደንት በመኾን የሀገሪቱ ነፃነት የተበሰረበት ነሐሴ 1960 ሌላው በአፍሪካ የተሰማው ድንቅ ዜና ነበር። እንደ አለመታደል ኾኖ ይህ የነፃነት ፌሽታ ብዙም ሳይቆይ ቻድ በከፋ የርስ በርስ ጦርነት አዘቅት ውስጥ ወድቃለች።

👉 የጦርነት ጦስ
አቶሚክ ቦምብ የሰው ልጅ እርስ በእርሱ በሚያደርገው የጦር መሳሪያ ፉክክር ውስጥ ከፈጠራቸው አውዳሚ ግኝቶች አንዱ ነው። ይህ ጸረ-ሕይዎት መሳሪያ ጥቅም ላይ የዋለው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነበር፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጃፓን፣ ጀርመን እና ጣሊያን በአንድ ላይ አብረው ኃይላቸው እየፈረጠመ መጣ፡፡ ይባስ ብሎም ጃፓን የአሜሪካን የባሕር ወደብ ደበደበች፡፡

ድሮም በቋፍ ላይ የነበረችው አሜሪካ የበላይነትን ለማግኘት የታጠቀችውን ጅምላ ጨራሽ የአቶሚክ ቦምብ ለመጠቀም ወሰነች። ልክ በዚህ ሳምንትም ከ300,000 ሕዝብ በላይ የሚኖርባትን የጃፓን ናጋሳኪ ከተማ በአቶሚክ እና ሐይድሮጅን ቦምብ ደበደበች፡፡በዚህም እነጀርመን እና ጣሊያንን “ነግ በኔ ” አስደነገጠቻቸው፡፡

ናጋሳኪ ከተማን ያወደመውን ቦምብ የጣለው “ቦክስካር” የተሰኘ ቢ 29 አውሮፕላን ነበር፡፡ ከመቅጽበትም በሺህ የሚቆጠር ሕይዎት ያለው ፍጡር ጠፍቷል ሲል ቶክዮ ታይምስ አስነብቧል፡፡ አደጋው በደረሰበት ወቅት በናጋሳኪ ከተማ ከ300,000 ሕዝብ በላይ ይኖርባት ነበር፡፡ «ፍንዳታው ከፍተኛ አዉሎ ንፋስ እና የዉኃ መጥለቅለቅ ያለበት አንድ ሺህ እጥፍ ከኾነ ሱናሚ ይበልጣል » ሲል ቶክዮ ታይምስ ጨምሮ አስነብቧል፡፡

በፍንዳታውም በአንድ ጊዜ የመቶ ሺህ ያህል ሕዝብ ሕይዎት ተቀጠፈ። የናጋሳኪ ምድርም 30 በመቶው ሕይወት አልባ ኾነ። ናጋሳኪ ከተማ የተደበደበችበት የአቶሚክ እና ሐይድሮጅን ቦምብ ጦስ እስከዛሬ ድረስ በተዘዋዋሪ መንገድ የከተማዋን ሕዝብ እየጎዳ ይገኛል፡፡ ጨቅላ ሕጻናት ሲወለዱ አካል ጉዳተኛ እየኾኑ ነው፡፡ የከባቢው መበከል ዛሬም ድረስ ዳፋው ለትውልዱ እየተሻገረ ይገኛል፡፡ የዕድሜ ባለጸጋዎች ለካንሰር እየተዳረጉ ነው፡፡ ሴቶች በዚህ ምክንያት እየመከኑ ነው፤ ሴቶች ያለዕድሜያቸው ያርጣሉ፡፡

ጃፓኖች “በእኛ የደረሰ በማንኛውም ሀገር እንዲደርስ አንፈልግም!” የሰርክ መፈክራቸው አድርገው እየተገበሩት ይገኛሉ፡፡ ዛሬ ብረት ወድረው ፣ ኒውክሌየር እያወዛወዙ፣ አቶሚክ መሳሪያ እያዘጋጁ ለጦርነት የሚዘጋጁ ሀገራትስ ምን አለ ከናጋሳኪ የኋላ ታሪክ ቢማሩ?

#ሳምንቱበታሪክ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም በጀግኖች ልጆቿ የከበረ ተጋድሎ ስሟ በዓለም መድረክ ከፍ ብሎ መታየቱ ነገም ይቀጥላል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleለውጥን ለምን እንፈራለን?