
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) የትምህርት ተቋማትን እና የመሥሪያ ቤቶችን ማኅተሞች በመጠቀም ሐሰተኛ ማስረጃ ሲሰጥ የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡
ተጠርጣሪው ግለሰብ ድርጊቱን ሲፈጽሙ ነበር የተባለው በአማራ ክልል ደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ቀበሌ 08 ስታዲየም አካባቢ ነው፡፡ ከኅብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሠረትም ዛሬ ከቀኑ 5:30 የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመያዝ ፖሊስ ፍተሻ አካሂዷል፡፡ እንደፖሊስ መረጃ ተጠርጣሪው 71 የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የግርጌ እና የራስጌ ማኅተሞች ተገኝውበታል፡፡
የተገኙት ማኅተሞችም የአልፋ ዩኒቨርሲቲ የዲግሪ የትምህርት ማስረጃ፣ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት የስልጣን ማኅተም፣ የተለያዩ የቀበሌ አስተዳደሮች ማኅተሞች፣ የአዲስ አበባ ወረዳ 9 ወሳኝ ኩነቶች ማኅተም፣ የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ማኅተም፣ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ማኅተሞች መሆናቸውን የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ገልጧል፡፡
የተለያዩ የመንጃ ፈቃድ ማረጋገጫዎች፣ የቤት ማኅበራት ማደራጃ ቅጾች፣ የ1ዐኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ካርድ፣ የውጤት መግለጫ እና የ8ኛ ክፍል ሐሰተኛ ትምህርት ማስረጃ መስጫ ካርድ ከተጠርጣሪው ቤት መገኘታቸውንም ነው ፖሊስ የገለጸው፡፡
የሐሠተኛ ማስረጃዎቹን የሚሠራበት ዴስክ ቶፕ ኮምፒዩተር እንዲሁም አንድ ሽጉጥ ከሰባት ጥይቶች ጋር ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ጉዳዩ በምርመራ እየተጣራ መሆኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ክፍል አስታውቋል፡፡
ኅብረተሰቡ እንደዚህ ዓይነት ወንጀልን በማጋለጥ የመንግሥትን ሀብት እና የሕዝብን ንብረት ከምዝበራ እንዲጠብቅም የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ጥሪ አቅርቧል፡፡
ምንጭ፡- አማራ ፖሊስ ኮሚሽን