
ደሴ: ነሐሴ 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ከስተመር ኤክስፔሪያንስ እና ኳሊቲ ማኔጅመንት ኦፊሰር ሰለሞን አበራ በሀገር አቀፍ ደረጃ 100 የኔትወርክ ትስስር ተግባራዊ መኾኑን ጠቁመዋል።
በኔትወርክ ትስስሩም 903 ሺህ የሚኾኑ የኀብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚኾኑም ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚሠራው ሥራ ዛሬ 305 የገጠር ቀበሌዎችን አዲስ የኔትወርክ ተጠቃሚ አድርጓል ነው ያሉት።
የኔትወርክ ትስስር ከተፈጠረላቸው አካባቢዎች መካከል ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን የቃሉ ወረዳ አዳሜ 025 ቀበሌ አንዱ ነው።
የአካባቢው ነዋሪዎች የኔትወርክ ትስስሩ ተጠቃሚ በመኾናቸው ደስታቸውን ገልጸው ለዓመታት የቆየ ጥያቄያቸው ምላሽ እንዳገኘም ተናግረዋል።
የቃሉ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሙሕዲን አሕመድ አዲሱ ሥራ ከ40 ሺህ በላይ የማኀበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸው የማኀበረሰቡን አኗኗር በማዘመን በኩል የሚሰጠው ጥቅምም ከፍተኛ መኾኑን አብራርተዋል።
ዘጋቢ፦ ሕይወት አስማማው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!